በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሆስፒታል እና ጤና ጣቢያዎችን ትስስር ለማጠናከር እየተሰራ ነው

59

አሶሳ፣  ጥር 15/ 2013(ኢዜአ) የሆስፒታል እና ጤና ጣቢያዎችን ትስስር በማጠናከር የእናቶች እና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ገለጸ። 

በሥራው ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ለጤና ባለሙያዎች የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በአሶሳ ከተማ ተካሄዷል።

በቢሮው የእናቶችና ህጻናት የስርዓተ ምግብ ዳይሬክተር አቶ አብዱልሙኒዬም አልበሽር በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የወሊድ ወቅት የእናቶች እና ህጻናት ሞት አሁንም አለ፡፡

ችግሩን ለመቀነስ ቢሮው የሆስፒታል እና ጤና ጣቢያዎች እንዲተሳሰሩ በማድረግ አገልግሎታቸውን ለማጠናከር እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

በሆስፒታል ጤና ጣቢያ ትስስር ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የተሻለ ልምድ ያላቸው የአሶሳ እና ፓዌ ሆስፒታሎች በሥራቸው የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ወደ ጤና ጣቢያዎች በመውረድ የስድስት ወራት ስምምነት በማድረግ በተግባር የተደገፈ የአቅም ግንባታ ድጋፍ እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የተገኘው ውጤትም በየጊዜው እንደሚገመገም ጠቁመዋል፡፡

ዓላማውም ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሆስፒታሎቹ ሲጓጓዙ የሚጎዱ እናቶችን እና ህጻናትን ለመታደግ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በጤና ተቋማቱ ትስስር ውጤት መታየት ጀምሯል ብለዋል፡፡

ጤና ጣቢያዎች አለአግባብ ወደ ሆስፒታሎች የሚልኳቸው እናቶች ቁጥር መቀነሱን የጠቀሱት አቶ አብዱልሙኒዬም ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀዋል፡፡

የአሶሳ አጠቃይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ከማለዲን አልፈኪ በበኩላቸው በሆስፒታሉ በወሊድ አገልግሎት የእናቶች እና ህጻናት ሞት የሚከሰትበት አጋጣሚ መኖሩን ገልጸዋል፡፡

ሆስፒታሉ በአሶሳ ዞን በረጅም ርቀት ላይ የሚገኙ ጤና ጣቢያ ባለሙያዎችን አቅም በማብቃት ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ወላድ እናቶችን መጠን ለመቀነስ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ይህም የሆስፒታሉን ጫና በመቀነስ አገልግሎቱን እንደሚያሻሽል ተናግረዋል፡፡

በሥልጠና ከተሳተፉ ጤና ባለሙያዎች  መካከል አቶ ሰብስቤ ጌታነህ  በተለይ በወሊድ ወቅት የሚደርሰውን የእናቶች እና ህጻናት ሞት ለመቀነስ በቁርጠኝት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ በአሶሳ ዞን የሚገኙ 50 የጤና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም