በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ በሚደረገው ጥረት ጋዜጠኞች ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ በሚደረገው ጥረት ጋዜጠኞች ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
ጥር 14/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ በሚደረገው ጥረት ጋዜጠኞች ትኩረት ሰጥተው በመስራት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተጠቆመ።
በትግራይ ክልል የተካሄደውን ህግ ማስከበር የህልውና ዘመቻ ላይ ሙያዊ ድጋፍ ላደረጉ ጋዜጠኞችም እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ሹፌሮች፣ በትግራይ ክልል ጉዳት የደረሰባቸው ሚዲያ ተቋማትን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት የሄዱ የቴክኒክ ቡድን አባላትም እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በአውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብሩ ላይ ግንባር በመገኘት የዘገቡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ፣ ዋልታ መረጃ ማዕከልና ከግል ሚዲያ ደግሞ የኢሳት ቴሌቪዥን እውቅና ከተሰጣቸው መካከል ናቸው።
ለጋዜጠኞቹ የተሰጠው እውቅና እስካሁን ላበረከቱት ምስጋና ለማቅረብና በቀጣይ በአገሪቷ ላሉ ትላልቅ አጀንዳዎች ተጨማሪ ኃላፊነት ለመስጠት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንደተናገሩት፤ በህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት መገናኛ ብዙሃን በተቀናጀ መንገድ መስራታቸው ትክክለኛ መረጃ ለኢትዮጵያም ለዓለም ህዝብም እንዲደርስ አድርጓል።
ሰራዊቱ የፈጸመውን የጀግንነት ተግባር በስራችሁ ማሳወቃችሁ የሚያኮራና የሚያሰመስግን ተግባር ነውም ነው ያሉት።
አሁን ቀጣዩ የቤት ስራ የትግራይ ህዝብ ምን ያስፈልገዋል? የሚለውን በትኩረት በመለየት ለመንግስትም እንዲደርስ ማድረግ መሆኑን ተናግረው በክልሉ የሚቀርቡ ሰብአዊ እርዳታዎች በተገቢው መንገድ እንዲደርስ ሙያዊ ኃላፊነታችሁን በብቃት መወጣት አለባችሁ ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው ባለሙያዎች በትግራይ ክልል የሚካሄደውን የመድሃኒት፣ ምግብና ሌሎችም አስፈላጊ ድጋፎች መድረሳቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በተለይም በቀጣይ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች መኖራቸውን አስታውሰው ግብርና፣ ገበታ ለሃገርና ምርጫ ላይ በትኩረት እንዲሰሩም ጠይቀዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ደኤታ ፍሰሃ ወልደሰንበት በበኩላቸው የጁንታው ቡድን በተለይም መጀመሪያ አከባቢ የተሳሳቱ መረጃ ያሰራጭ አንደነበር አስታውሰዋለ።
በስፍራው የተገኙ ባለሙያዎች ግን ከቦታው ትክክለኛ መረጃ በማድረስ ኀብረተሰቡ እንዳይደናገር በማድረግ አይነተኛ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል።
የብሮድ ካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንደተናገሩትም በዘመቻው ላይ የተሳተፉ ጋዜጠኞች ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ለህዝቡ መረጃ ማቀበላቸው የመገናኛ ብዘሃንን ተአማኒነት ከፍ ያደረገ ነው።
በዘመቻው ላይ አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላት የተሰጠው እውቅና የኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከቤይ ኢትዮጵያ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው።