ቀጥታ፡

በአፋር ክልል የጋላፊ ዲቾቶ መገንጠያ ኤሊዳር በሌሆ አስፋልት ሲሚነቶ ኮንክሪት መንገድ ተመረቀ

ጥር 14 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የጋላፊ ዲቾቶ መገንጠያ ኤሊዳር በሌሆ አስፋልት ሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

መንገዱን የክልሉ ፕሬዚዳንት አወል አርባ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ እና ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ነው የተመረቀው።

የ78 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የመንገድ ግንባታ ለማጠናቀቅ 4 አመት ተኩል የፈጀ ሲሆን 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል።

በምረቃው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ "መንገዱ ከጎረቤት አገሮች ጋር በወደብ አማካኝነት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማሳለጥ ያግዛል" ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊ ሞገስ እንደተናገሩት ደግሞ የመንገዱ መገንባት በአፋር ክልል ያለውን ከፍተኛ መጠን ያለው የፖታሽ ማዕድን ለአለም ገበያ በቀላሉ በማቅረብ አገሪቱን ተጠቃሚ ያደርጋታል፡፡

የክልሉ ፕሬዚዳንት አወል አርባ በበኩላቸው ፕሮጀክቱን የአፋር ክልል በሚገባ እንደሚከባከበው አረጋግጠዋል።

መንገዱ ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን በመጠቀም ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንድታገኝ የሚያግዝ መሆኑም ተገልጿል።

በዚሁ ወቅት ሜሎዶኒ መገንጠያ ማንዳ ቡሬ የአስፋልት ሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

መንገዱ 71 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ ይጠይቃል።

የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅም ወደ አሰብ ወደብ ለመግባት ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም