የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚዬር ሊግ አንደኛ ዙር ጨዋታ በሐዋሳ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚዬር ሊግ አንደኛ ዙር ጨዋታ በሐዋሳ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ጥር 14/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚዬር ሊግ የአንደኛ ዙር ውድድር መርሃ ግብር ከፊታችን እሁድ ጀምሮ በሐዋሳ ከተማ ይካሄዳል።
የጤና ሚኒስቴር የኮቪድ -19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው ፕሮቶኮል መሰረት የሊጉ ጨዋታዎች በዝግ ሜዳ በባህር ዳር፣ ሐዋሳና አዲስ አበባ ከተሞች እንዲደረጉ ወስኗል።
በዚህም መሰረት የዙሩ የመጀመሪያ አራት ሳምንት ጨዋታዎች ከታህሳስ 10 እስከ 23 ቀን 2013 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።
ከሶስት ሳምንት እረፍት በኋላ የሊጉ ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ በሐዋሳ ከተማ ይቀጥላሉ።
በአምስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከነገ በስቲያ ጠዋት 2፡30 የሊጉ መሪ መከላከያ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጋር ይጫወታል።
መከላከያና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።
በተመሳሳይ እሁድ ከጠዋቱ 3፡45 በአራት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፌዴራል ፖሊስ በሶስት ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ጋር ይጫወታሉ።
ሰኞ ጥር 17 ቀን 2013 ከጠዋቱ 2፡30 ሚዛን አማን ከተማ ከአዲሱ የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ባህርዳር ከተማ እንዲሁም ከጠዋቱ 3፡45 ጎንደር ከተማ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በሐዋሳ ከተማ ከአምስተኛ አስከ ሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከጥር 16 እስከ 21 ቀን 2013 ይካሄዳሉ።
የሐዋሳው መርሃ ግብር ፍጻሜውን ካገኘ በኋላ ከስምንተኛ እስከ 10ኛ ሳምንት ያሉ ጨዋታዎች ከየካቲት 13 እስከ 26 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ይደረጋሉ።
የሊጉ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች በተመሳሳይ በሶስቱ ከተሞች እንደሚከናወን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በዘንድሮው የእጅ ኳስ ፕሪሚዬር ሊግ ዘጠኝ ክለቦች እየተሳተፉ ነው።
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚዬር ሊግ ባለፈው ዓመት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መቋረጡንና ውድድሩ ያለ አሸናፊ እንዲሰረዝ መደረጉ ይታወሳል።
ካለፈው ዓመት በፊት በተካሄዱ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች መከላከያ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አሸንፈዋል።