ቀጥታ፡

በአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የዳያስፖራው ሁለንተናዊ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ

አዲስ አበባ ጥር 14/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የዳያስፖራው ሁለንተናዊ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን አስታወቀ።

ዳያስፖራው ባለፉት ስድስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 89 ሚሊዮን ብር ማዋጣቱም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር  ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ለኢዜአ እንዳሉት የዳያስፖራው ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ  ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 89 ሚሊዮን ብር ማዋጣቱንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

ዳያስፖራው ባለፉት አምስት ዓመታት ከ550 ሚሊዮን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ መሰባሰቡንም አስታውሰዋል።

ለገበታ ለሀገር  እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችም የዲያስፖራው ተሳትፎ ማደጉን የገለጹት ዶክተር መሐመድ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚውል 500 ሚሊዮን ብር በጥሬ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እያደረገ ያለው ድጋፍም  ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ሁለት ፕሮጀክቶችን ለመስራት ተለይተዋል ብለዋል።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ አሁን ላይ በአገር ጉዳይ ላይ በባለቤትነት በመሳተፍ የላቀ እንቅስቃሴ ያሳየበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በእውቀት የማምረትና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች ላይም የዳያስፖራው ሚና እያደገ መጥቷል ብለዋል ዶክተር መሐመድ።

የክልል ዳያስፖራ  ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶችም ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ከሚያደርገው ተሳትፎ በተጨማሪ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አለም አቀፉን ማህበረሰብ በማስገንዘብ ረገድ ሚናቸውን እየተወጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የድሬዳዋ ዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አክሊለ ታጠቅ በበኩላቸው ዳያስፖራው የኮሮናቫይረስ መከላከልን ጨምሮ በተለያዩ ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች ጠንካራ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለተማሪዎች የደብተርና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንም አስታውሰዋል።

በተማሪዎች ምገባ ከ750 በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውንም  ኃላፊው ተናግረዋል።

ክልሉ ዳያስፖራውን ለማሳተፍ ባከናወናቸው ተግባራር ዳያስፖራው በተለያዩ መስኮች እየተሳተፈ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የዳያስፖራ መረጃና ጥናት ዳይሬክተር አቶ አህመድ ሙህዲን ናቸው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም