በታንዛንያ እስር ቤቶች የነበሩ 80 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ሊመለሱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በታንዛንያ እስር ቤቶች የነበሩ 80 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ሊመለሱ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 14/2013 ( ኢዜአ) በታንዛንያ እስር ቤቶች የነበሩ 80 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ በታንዛንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዮናስ ዮሴፍ ገለጹ።
በ2021 በእስር ቤቶቹ የሚገኙ 1 ሺህ 800 ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ መታሰቡንም አምባሳደሩ ጠቁመዋል።
በታንዛንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዮናስ ዮሴፍ፤ በዳሬሰላም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሕዳር ወር 2013 ዓ.ም በሞሮጎሮ፣ ታንጋ፣ ፕዋኒና ባጋሞዮ ግዛቶች ባደረገው ምልከታ ከ1 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በእስር ቤቶች እንዳሉ መግለፃቸው ይታወሳል።
ኤምባሲው በአራቱ ግዛቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ይቅርታ ተደርጎላቸው እንዲፈቱና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ከታንዛንያ የኢሚግሬሽንና ማረሚያ ቤት ተቋም ጋር ሲነጋገር መቆየቱንና ተቋሙም በጎ ምላሽ መስጠቱን አምባሳደሩ ተናግረዋል።
ተቋሙ ኤምባሲው ዜጎቹን ወደ አገር ቤት ለመመለስ የሚያስፈልገውን ገንዘብ አሰባስቦ ዝግጁ ሲሆን ኢትዮጵያዊያኑን ለመፍታት ፈቃደኛ እንደሆነም አመልክተዋል።
"ኤምባሲው ዜጎቹ ከእስር ተፈተው ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት የሀብት ማሰባሰብ ሥራ እያከናወነ ይገኛል" ብለዋል።
በታንዛንያ የሚገኘው የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም ) ቢሮ 80 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ገንዘብ እንደሚሸፍንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
በእዚህም 80 ኢትዮጵያዊያን ከእስር መለቀቃቸውንና በሁለት ሳምንት ጊዜ ወስጥ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ጠቁመዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፣ በአራቱ ግዛቶች ያሉ እስረኞች ተፈተው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የኢትዮጵያ መንግስት፣ ዳሬሰላም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትና ሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በጋራ እየሰሩ ነው።
"ኤምባሲው በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች የሰብአዊ መብታቸው መጠበቁንና አስፈላጊውን አገልግሎት እያገኙ ስለመሆኑ የቅርብ ክትትል እያደረገ ይገኛል" ብለዋል።
በአራቱ ግዛቶች ያሉትን ጨምሮ ከመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን 1 ሺህ 800 ዜጎች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ታንዛንያ እንደገቡና በእስር ላይ እንዳሉ ለማወቅ መቻሉንም አመልክተዋል።
በታንዛንያ እስር ቤት የሚገኙ 1 ሺህ 800 ኢትዮጵያዊያንን በፈረንጆቹ 2021 ሙሉ ለሙሉ ለመመለስ ኤምባሲው ማቀዱን ጠቁመዋል።
ለመመለስ የሚያስፈልገውን ወጪም በኢትዮጵያ መንግስትና በልማት አጋሮች እንደሚሸፈን ተናግረዋል።
አሁንም ወደ ታንዛንያ የሚገቡ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ የገለጹት አምባሳደር ዮናስ ዜጎች በጉዟቸው ወቅት በደላሎች እንግልትና ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን አመልክተዋል።
በርካታዎቹ ከደቡብ ክልል እየተነሱ መዳረሻቸውን ደቡብ አፍሪካ ለማድረግ በርካታ እንግልትና ስቃይ እየደረሰባቸው እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የሚሰደዱት ዜጎች ወጣቶች መሆናቸውን የገለጹት አምባሳደር ዮናስ "በትንሹ ለደላሎች እስከ 150 ሺህ ብር ይከፍላሉ" ብለዋል።
ወጣቶቹ በሚከፍሉት ገንዘብ በሚኖሩበት አካባቢ ኑሯቸውን ለማሻሻል እንደሚችሉና በዚህ ላይ መንግስት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት ተቋማትና የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው የአመለካከት ለውጥ ላይ ቢሰሩ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚመጣ አክለዋል።
ከሁለት ዓመታት በፊት በዳሬሰላም የተከፈተው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከ3 ሺህ በላይ ዜጎችን ከእስር አስፈትቶ ወደ አገር ቤት መመለሱን አስታውቋል።