የጅማ አባጅፋር ስፖርት ክለብ በውጤታማነቱ እንዲቀጥል ሕዝባዊ ድጋፍ ያስፈልገዋል----የክለቡ ሥራ እስኪያጅ - ኢዜአ አማርኛ
የጅማ አባጅፋር ስፖርት ክለብ በውጤታማነቱ እንዲቀጥል ሕዝባዊ ድጋፍ ያስፈልገዋል----የክለቡ ሥራ እስኪያጅ
ጅማ ግንቦት 4/2010 የጅማ አባጅፋር ስፖርት ክለብ በውድድር እያሳየ ያለው ውጤታማነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተደራጀ የሕብረተሰብ ድጋፋ አስፈላጊ መሆኑን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ። የክለቡ አጠቃላይ ጉባኤ ዛሬ በጅማ ከተማ ተካሂዷል ። የጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ስፖርት ክለብ ሥራአስኪያጅ አቶ ኢሳያስ ጅራ የክለቡን የ2010 በጀት ዓመት የአስር ወር የሥራ አፋጻጻም ለጠቅላላው ጉባኤ ባቀረቡበት ውቅት እንደገለጹት፣ የጅማ ከተማ አስተዳደር በገንዘብና በአመራር ያደረገው ድጋፍ ለክለቡ መጠናከርና ውጤታማነት አሰተዋፆ አድርጓል ። "ክለቡ ውጤታማነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፉን ህዝባዊ መሰረት ማስያዝ ያስፈልጋል " ብለዋል ። ክለቡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን በአንደኛ ደረጃ እየመራ እንደሚገኝና የኮኮብ ጎል አግቢነቱን ደረጃም በቡድኑ ተጫዋቾች የተያዘ መሆኑን ለውጤታማነቱ በማሳያነት ጠቅሰዋል ። "በስፖርታዊ ጨዋነትም ከቅድስ ጊዮርጊስ፣ ድሬዳዋና መቀሌ ክለቦች ቀጥሎ በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል" ብለዋል አቶ ኢሳያስ፡፡ ጅማ አባጅፋር በቀጣይም ውጤታማነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሕብረተሰቡ፣ የከተማው አሰተዳደር፣ ምክርቤቱና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በገንዘብና በሞራል እያደረጉ ያለውን ፍጋፍ በተደራጀ መልኩ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። እንደ አቶ ኢሳያስ ገለጻ፣ ለክለቡ ለ2010 በጀት ዓመት ከተመደበለት 42 ሚሊዮን ብር በጀት ውስጥ 30 ሚሊዮኑ በጅማ ከተማ አስተዳደር ቀሪው ደግሞ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተሸፈነ ነው። "ባለፉት አስር ወራት ለክለቡ እንቅሰቃሴ 31 ሚሊዮን ብር ውጭ ተደርጓል " ሲሉም ለጉባኤው አመልክተዋል። የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መክዩ መሀመድ "ክለቡ በገንዘብም ሆነ በአመራር ከከተማ አስተዳደሩ ጥገኝነት መላቀቅ ይገባዋል" ብለዋል፡፡ ቡድኑ ውጤታማነቱን በማይጎዳ መልኩ ሕዝባዊ መሰረት እንዲይዝ አስተዳደሩ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም አረጋግጠዋል። በኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሁሴን ዝናብ በበኩላቸው ክለቡ ውጤታማ እንዲሆን የክልሉ መንግስት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት። "ክለቡ ለፕሪሚየር ሊጉ አዲስ ቢሆንም ውጤታማ መሆን የቻለው በአመራሩ፣ በአስልጣኞችና በተጫዋቾች ጠንከራ የተቀናጀ ሥራ ነው" ያሉት ደግሞ የክለቡ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ናቸው። የክለቡ ስፖርት ቤተሰብ የመተሳስብ፣ የመረዳዳትና የመቻቻል ባህልን እንዲያዳብር ጠይቀዋል። ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል አቶ ቴዎድሮስ ደበላ በሰጡት አስተያየት " ክለቡ በከተማው ማዘጋጃ ቤት ገቢ ላይ ጥገኛ የሆነው የክለቡ አመራሮች ከሕብረተሰቡ የሚገኝ ሃብት ላይ በትኩረት መስራት ስላልቻሉ ነው" ብለዋል። የስፖርት ክለቡ አመራር ሕብረተሰቡ ክለቡን የሚደግፍበትን ህጋዊ አሰራር መዘረጋት እንደሚገባው አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመዋል። አቶ ጧሊብ ረሸድ በበኩላቸው "ክለቡ ከስታዲዬም ያገኘው ገቢ ከ300 ሺህ ብር ያልበለጠ መሆኑ የአመራሩ ገቢ የመሰብሰብና የማስተዳደር አቅም ዝቅተኛ መሆኑን ማሳያ ነው "ብለዋል። በሁሉም ጨዋታዎች ስታዲዮሙ በተመልካች እየሞላ ባለበት ሁኔታ ከዘርፉ አነስተኛ ገቢ የመሰብሰቡ ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባ ጠቁመዋል። "የጅማ ከተማ ህዝብ ክለቡን በገንዝብ ሆነ በሞራል ለመደገፍ ፈቃደኛ መሆኑ ይታወቃል "ያሉት አቶ ጧሊብ በአመራሩ በኩል ያለው ያለማስተባበር ችግር ሊታሰብበትና ሊሻሻል እንደሚገባ አመላክተዋል ።