ለትግራይ ክልል 71 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችና የህክምና ግብዐቶች ተልከዋል - የጤና ሚኒስቴር

157

አዲስ አበባ፣ ጥር 14/2013 ( ኢዜአ) በትግራይ ክልል ለደረሰው አስቸኳይ ሁኔታ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እስካሁን ከ71 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችና የህክምና ግብዐቶች መላካቸውን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ግብዓቶቹ በክልሉ ለሚገኙ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ማዕከላት በመላክ ለሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች በመሰራጨት ላይ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።

ለደረሰው አስቸኳይ ሁኔታ ፈጣን ምላሽ ለመስጠትም የተለያዩ የጤና ባለሙያዎች የያዘ ቡድን ወደ ትግራይ መላኩን ጠቅሷል።

ሚኒስቴሩ፣ ተጠሪ ኤጀንሲዎቹ እና የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ከሰብዓዊና ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር በትግራይ ክልል ድጋፍ እና መልሶ ማቋቋም ላይ በስፋት እየሰሩ እንደሚገኙም በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አመልክቷል።

“በተጎዱ አካባቢዎች ያለው የህብረተሰብ ጤና እና ደህንነት ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ሲሆን መንግስት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የድንገተኛ ምላሽ እየሰጠና ወገኖች ወሳኝ የጤና አገልግሎቶች እንዲያገኙ ለማድረግ ላለፉት በርካታ ሳምንታት እየሰራ ይገኛል” ሲል ሚኒስቴሩ አስታውሷል።

ተቋማት የሚሰጡት መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስቀጠል ከሕክምና አቅርቦቶችና መድኃኒቶች በተጨማሪ አምቡላንሶችን ጨምሮ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነም ገልጿል።

በማህበረሰቡ ውስጥ የበሽታ ቅኝትና የተንቀሳቃሽ ክሊኒከ አገልግሎቶችም በአንዳንድ አካባቢዎች ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየተሰጠ እንደሆነም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም