በክልሉ 4 ሚሊዮን የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል-ቢሮው

78

ሐዋሳ፣ ጥር 13/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል 4 ሚሊዮን የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የበጋ ወቅት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ መለሰ መና ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮ በጋ ወቅት 3 ሺህ 284 ንዑስ ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ  ለማካሄድ ታቅዷል።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው  357 ሺህ ሄክታር መሬት ባካለለ መልኩ እንደሚከናወን አመላክተዋል ።

በዘመቻ በሚከናወነው ስራው 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የሚያስችሉ ጉድጓዶች ተቆፍረው እንደሚዘጋጁ ለአብነት ጠቅሰዋል ።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው እንደ ሃገር የብልጽግናን ጉዞ  ለማፍጠን የተጀመሩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከደለልና መሰል ችግሮች ለመከላከል የሚኖረውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።

ለአንድ ወር በሚቆየው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራውን ለማካሄድ የተፋሰስ ጥናት፣ የቦታ መለየትና ስልጠና የመስጠት የመሳሰሉ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል ።  

በክልሉ ባለፉት 11 አመታት በተከናወነ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት ለጉዳት የተጋለጠ  መሬት መልሶ በማገገም ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

የመሬት ለምነትንና የደን ሃብትን በማሻሻል  ምርታማነትን እንዲሁም ለምርታማነት መጨመር አስተዋጾ ማድረጉን የቢሮው ምክትል ሀላፊ አስታውቀዋል።

በክልሉ የዘንድሮ የበጋ ወቅት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከፊታችን ጥር 18 ቀን 2013 ዓ.ም ተጀምሮ ለአንድ ወር በዘመቻ እንደሚካሄድ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም