በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም የተመራ የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ዛሬ ዚምባቡዌ ይገባል

60
አዲስ አበባ ሃምሌ 17/2010 በቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የተመራ የዚምባቡዌ የፕሬዚዳንታዊና ምክር ቤቶች ምርጫ የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ዛሬ ዚምባቡዌ ይገባል። ዚምባቡዌ ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓ.ም የፕሬዚዳንታዊና ምክር ቤቶች ምርጫ ታካሂዳለች። የምርጫውን አጠቃላይ ሁኔታ የሚመመለከት በአቶ ሃይለማርያም የተመራ የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ዛሬ ከሰአት በኋላ ዚምባቡዌ እንደሚደርስ የአፍሪካ ህብረት በድረ ገጹ አስፍሯል። አቶ ሃይለማርያም የሚመሩት ልዑክ ሮበርት ሙጋቤ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያ ከደረሱ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን የህብረቱ ልዑክ በዚምባቡዌ በሚደረገው ምርጫ ስለሚኖረው አጠቃላይ ቆይታ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም የምርጫው ታዛቢ ልዑክ መሪ ሆነው የተመረጡት በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት እንደሆነ ይታወሳል። የአፍሪካ ህብረት የምርጫ መታዘብ ተግባር የሚያከናውነው በተለያየ ጊዜ በህብረቱ በወጡ የምርጫ መመሪያዎች፣ ደንቦች፣ ህጎችና በዓለም አቀፍ ደረጃ በወጡ የምርጫ ታዛቢነት መርሆች ላይ በመመስረት እንደሆነ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም