ቀጥታ፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ፎረም በመቀሌ ከተማ እየተካሄደ ነው

መቀሌ ሀምሌ 17/2010 ህወሓትን ጨምሮ የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሳተፉበት  ፎረም  በመቀሌ ከተማ እየተካሄደ ነው። የፓርቲዎቹ ተወካዮችና የመቀሌ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎት እየተሳተፉበት ያለው ይሄው ፎረም ከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ  ነው፡፡ ከ40 ዓመታት በኋላ ከውጭ ሃገር ወደ ክልሉ መጥተው የወደፊት ዓላማቸው በፎረሙ ላይ ለተሳተፉ የመቀሌ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ካስተዋወቁት መካከል የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ይገኙበታል፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ዶክተር አረጋዊ በርሄ  እንዳሉት፣ ወደ ሃገር ውስጥ ገብተው አላማቸውን ለማራመድ የመጡት አሁን በሃገሪቱ በተፈጠረው ምቹ የዲሞክራሲ ለውጥ ምክንያት ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ጥቅም የሚረጋገጠው ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በጋራና በአንድነት ሲቆም ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። " አንድነት የተሻለ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት እድል ይሰጣል" ያሉት ዶክተር አረጋዊ፣ለዘላቂ ልማትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አሁንም ተባበሮ በመስራት እንደሚረጋገጥ ተናግረዋል። " በሃገሪቱ ውስጥ ቅይጥ የሶሻል ኢኮኖሚን የመገንባት ዓላማ አለን"  ያሉት ከፍተኛ አመራሩ፣አላማቸውን ለማስረጽ ከተወለዱበት የትግራይ ክልልን ጨምሮ በመላው የኢትዮጰያ ክፍሎች  እንደሚቀሳቀሱ አስታውቀዋል። ህወሓትን ወክለው የተናገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፣"አሁን በሃገሪቱ  የተፈጠረ ለውጥ ጥንካሬውን በመደገፍና ያሉትን ችግሮች በመንቀፍ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በእኩልነትና አንድነት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ሰላምና ኢኮኖሚን ለመገንባት የትግራይ ህዝብ ጠንክሮ መታገል አለበት" ብለዋል። በሃገሪቱ ላይ ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ የሚችለው ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን መጠበቅ ሲቻል መሆኑንም ገልጸዋል። የዓረና ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ " አሁን በሃገሪቱ የተፈጠረው ለውጥ የነጻነት፣ፍትህና እኩልነት ፍንጭ የሚሰጥ ነው" ብለውታል። አቶ አብርሃ እንዳሉት የትግራይ ህዝብ የልማትና የዲሞክራሲ ጥቅሞች በዘላቂነት እንዲረጋገጥ  ትክክለኛ የስትራቴጂና ታክቲክ የመታደገያ መስመሮች በሰከነ አኳሃን መምረጥ  ያስፈልጋል። በግል የቀረቡት የቀድሞ የህወሓት ታጋይ ጀኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ በበኩላቸው፣" አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ህገ መንግስት ዘመናዊና የኢትዮጵያ ህዝቦች ጥቅም በእኩልነት ማስተናገድ የሚችል ነው "ብለዋል። ህገ መንግስቱ ባለፉት ዓመታት በጥቂት ባለስልጣናት ፍላጎት ሲጣስ መቆየቱን አስታውሰው፣"አሁን የተፈጠረው ለውጥ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን ወደ ትክክለኛ ጉዞ እንዲያመራ ህገ መንግስቱን የማይታለፍ ቀይ መስመር ማድረግ እንደሚገባም ይገባል " ሲሊ አመልክተዋል፡፡              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም