የአባያ ወረዳ ፖሊስ 278 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዥ እጽ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአባያ ወረዳ ፖሊስ 278 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዥ እጽ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ

ነገሌ፣ ጥር 13/2013( ኢዜአ) በምዕራብ ጉጂ ዞን የአባያ ወረዳ ፖሊስ በተሽከርካሪ ተጭኖ ወደ ሞያሌ ሲጓጓዝ የነበረ 278 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዥ እጽ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ።
የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሻምበል ደረሰ እንዳሉት አደንዛዥ እጹ በቁጥጥር ሥር የዋለው ከሀዋሳ ወደ ኬንያ ሞያሌ ከተማ እየተጓጓዘ በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ሰመሮ ቀበሌ ሲደርስ ነው፡፡

ፖሊስ አደንዛዥ እጹንና ሲጓጓዝበት ከነበረው ተሽከርካሪ ጋር ጥር 11/2013 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የአደንዛዥ እጹን በአዘዋዋሪነት የተጠረጠረው ግለሰብ ለጊዜው ከአካባቢው ሸሽቶ ቢያመልጥም ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለመቆጣጠር ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በህዝብ ጥቆማ በቁጥጥር ሥር የዋለው አደንዛዥ እጹ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ያመለከቱት የፖሊስ አዛዡ የእጹ ዓይነት ለመለየት ለፌዴራል ፖሊስ ፎረንሲክ ምርመራ እንደሚላክ ገልጸዋል።
የወረዳው ዋና አስተዳደር አቶ አያኖ አለማየሁ በበኩላቸው ህገ ወጥ እንቅስቃሴን ለመከላከል ከግለሰብ እስከ መንግስት ተሽከርካሪዎች የተጠናከረ ፍተሻና ቁጥጥር በመደረግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ህገ ወጥነትን ለማስቀረት በእሳቸው የሚመራና የተለያዩ አካላትን ያካተተ ኮሚቴ መቋቋሙንም ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው ህብረተሰብ ህገ ወጥ እንቅስቃሴን በማጋለጥ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል ከወረዳው ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡
በምዕራብ ጉጂ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት 22 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው አደንዛዥ እጽና የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን በመጥቀስ የዞኑ ፖሊስ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዲቪዥን ሀላፊ ዋና ሳጂን ፈዬራ ከይረዲን ለኢዜአ ጨምረው ገልጸዋል።