በጎንደር ጥምቀት በዓል ላይ የስርቆት ወንጀል በመፈጸም የተከሰሱ 6 ግለሰቦች በእስራት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው

90

ጎንደር፣ ጥር 13/2013(ኢዜአ) በጎንደር ከተማ በጥምቀት በዓል ላይ የስርቆት ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ተይዘው የተከሰሱ ስድስት ግለሰቦች ከ9 ወር እስከ ሁለት ዓመት ከ6 ወራት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር አቃቢ ህግ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ግለሰቦቹ የእስራት ቅጣቱ የተወሰነባቸው በከተማዋ በሚገኘው ጥምቀተ ባህር ውስጥ በተቋቋሙ ሁለት ጊዜያዊ ችሎቶች አማካኝነት መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ግርማ ጌታቸው ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

በጥምቀት በዓሉ ላይ የታዳሚዎችን ሞባይል፣ ላፕ ቶፕ ኮምፒዩተርና አልባሳት ስርቆት ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ በመያዛቸው የእስራት ቅጣቱ ተላልፎባቸዋል ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተማ አስተዳደሩ በጥምቀት በዓል ግለሰቦች የጦር መሳሪያ ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ የጣለውን ገደብ የተላለፈ አንድ ግለሰብም በአንድ ዓመት እስራትና የ5ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንደተላለፉበት የጠቀሱት ሃላፊው መሳሪያውም ለመንግስት ገቢ እንዲሆን መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡

በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓል ከከተራ ጀምሮ ያለምንም የጸጥታ ችግር በሠላም መከበሩንም ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም