በዛሬው የሊጉ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ሲዳማ ቡናን ፋሲል ከነማ ደግሞ አዳማ ከተማን አሸነፉ - ኢዜአ አማርኛ
በዛሬው የሊጉ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ሲዳማ ቡናን ፋሲል ከነማ ደግሞ አዳማ ከተማን አሸነፉ
ጅማ፣ጥር 12/ 2013 (ኢዜአ) በጅማ ዛሬ በተካሄደው ስምንተኛው ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ሲዳማ ቡናን ሁለት ለዜሮ ፋሲል ከነማ ደግሞ አዳማ ከተማን አራት ለዜሮ አሸነፉ፡፡
በጥዋቱ የጨዋታ መርሀ ግብር ለሀዋሳ ከተማ ብሩክ በየነ ባስቆጠራት ግብ ከመጀመሪያው ሲመራ መስፍን ታፈሰ በ90ኛው ደቂቃ ሁለተኛዋን ጎል አክሎ ጨዋታውን ሁለት ለዜሮ ማሸነፍ ችሏል፡፡
ከሰዓት በኋላ የፋሲል ከነማና አዳማ ከተማ ጨዋታ ቀጥሎ በ48ኛው እና 74ኛው ደቂቃ ሙጂብ ቃሲም ሁለት ጎሎችን ለፋሲል ከነማ አስቆጥሯል፡፡
በ72ኛው ደቂቃ ይሁን እንዳሻው እና በ85ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ናትናኤል ወልደ ጊዮርጊስ አራተኛዋን ጎል ከመረብ አሳርፏል፡፡
በዚህም አጼዎቹ 19 ነጥብ ሰብስበው አንደኛ ደረጃን አስጠብቀዋል፡፡
ፋሲል በ19 ነጥብ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ15 ነጥብ እና ባህርዳር በ13 ነጥብ በቅደም ተከተል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
የነገው የጨዋታ ፕሮግራም እንደሚያመለክተው ረፋድ አራት ሰዓት ላይ ድሬድዋ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና የሚገናኙ ሲሆን ዘጠኝ ሰዓት ደግሞ ጅማ አባ ጅፋር ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማል፡፡