ቀጥታ፡

ኤጀንሲው ባለፉት ስድስት ወራት ከ130 በላይ ሀሰተኛ ሰነዶችን መያዙን አስታወቀ

አዲስ አበባ ጥር 12/2013 (ኢዜአ) የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ ኤጀንሲ ባለፉት ስድስት ወራት ከአንድ መቶ ሰላሳ በላይ ሀሰተኛ ሰነዶችን መያዙን አስታወቀ።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የተጠሪ ተቋማቱን የስድስት ወር የዕቅድ አፈፃፀም ዛሬ ገምግሟል።

በመድረኩም የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ ኤጀንሲ፣ የሲቪል ማህበረስብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ፣ የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን፣ የፌዴራል ፍትህ፣የህግ ምርምርና ስልጠና ኢንሲትቲዩት እንዲሁም የኢትዮጵያ አዕምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት አፈጻጸማቸውን አቅርበዋል።

የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ በዚህን ወቅት ኤጀንሲው ባለፊት ስድስት ወራት 139 ሀሰተኛ ሰነዶች መያዙን ተናግረዋል።

ከተያዙት ሀሰተኛ ሰነዶች መካከል 62 በመቶ የሚሆኑት የተለያዩ ሀሰተኛ መታወቂያዎች መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

ሀሰተኛ መታወቂያዎቹ በዋናነት ውክልና በመውሰድ ባለቤት ያልሆኑበትን ንብረት ለመጠቀምና ለመሸጥ እንዲሁም ከባንኮች ገንዘብ ለማውጣት ሙከራ ሲደረግባቸው መያዛቸውንም አብራርተዋል።

ኤጀንሲው ከባንኮች ጋር በበይነ-መረብ በመተሳሰር በሀሰተኛ ሰነድ የሚደረግ የገንዘብ ዝውውር ሙከራን ለመቆጣጠር እየሰራ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

በተጨማሪ ለባለትዳር ሰዎች ትዳር እንደሌላቸው ተደርጎ የተሰሩ ሀሰተኛ ሰነዶች መያዛቸውንም አንስተዋል ።

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነር ጄኔራል ጀማል አባሶ በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ወራት የማረሚያ ቤቶችን የጥበቃ አደረጃጀት ማሻሻል መቻሉን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም አንድ መደበኛ የጥበቃ አደረጃጀት እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ከመደበኛ ጥበቃ በተጨማሪ አድማ ብተና፣ እጀባ የሚሰጡና ፈጥኖ ደረሽ ሃይል በሚል አራት አደረጃጀቶች መዋቀራቸውን ገልጸዋል።

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ባለፉት ስድስት ወራት ተጠሪ ተቋማት የተሻሉ ስራዎች በማከናዎናቸውን ገልጸው፤ ይህን ጠንካራ ጎን ይዘው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።

በቀጣይ ስድስት ወር ለተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም