ኢትዮጵያ ባሏት የቱሪዝም መደረሻዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም የተሻለ የመጎብኘት እድል አላት - የውጭ ቱሪስቶች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ባሏት የቱሪዝም መደረሻዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም የተሻለ የመጎብኘት እድል አላት - የውጭ ቱሪስቶች
አዲስ አበባ ጥር 12/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ብዛት ባላቸው ድንቅ የቱሪዝም መደረሻዎቿ ምክንያት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም ቢሆን የተሻለ የመጎብኘት እድል እንዳላት ኢዜአ ያነጋገራቸው የውጭ አገራት ዜጎች ገለጹ።
በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም በቻይና ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ የመጀመሪያው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተገኘበት ጊዜ አንስቶ ወረርሽኙ በፍጥነት በመዛመት ብዙዎችን አጥቅቷል፤ የብዙዎችን ሕይወትም ነጥቋል።
አገሮች ወረርሽኙን ለመከላከል ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል እንቅስቃሴን በመዝጋትና በመገደባቸው የቱሪዝም ዘርፉን መጉዳቱንና የተባበሩት መንግስታት የቱሪዝም ድርጅት መረጃ ያሳያል።
በተጠናቀቀው የአውሮፓዊያን ዓመት ዓለም አቀፍ የቱሪስቶችን እንቅስቃሴ ከ58 እስከ 78 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ አገሮች ከዘርፉ ከ910 ቢሊዮን እስከ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ዶላር ማጣታቸውን ድርጅቱ ገልጿል።
ኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም ባሏት በርካታ ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች በተሻለ የመጎብኘት እድል አላት ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ አገራት ዜጎች ገልጸዋል።
ብዙ የቱሪዝምና የባህል ሀብቶች ባለቤት በመሆኗ ገና መታየት ያለባቸው በርካታ ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች አሏት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ባላት በርካታ የቱሪዝም ሐብት በምስራቅ አፍሪካ ካሉ አገሮች ዋንኛ የቱሪዝም መዳረሻ መሆን ተችላለችም ነው ያሉት።
ቱሪስቶች ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ወደ አውሮፓና አሜሪካ እንደሚሄዱ የገለጹት ጎብኚዎቹ፣ ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎችን ሊጎበኙ ይችላሉ ብለዋል።
እንግሊዛዊው ናይጀል ስዊት የአገሩ ዜጎች ኢትዮጵያን መጥተው የመጎብኘት ፍላጎት እንዳላቸው ገልፆ በእውቁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል የውጭ ዜጎች መጥተው እንዲጎበኙ ማስተዋወቅ ይቻላል ብለዋል።
በሁሉም አካባቢዎች ቱሪስቶችን ለመሳብ ደግሞ የቱሪዝም መዳረሻዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በአግባቡ መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል ።
የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ማጠናከርን ጨምሮ የቱሪስቱን እንቅስቃሴ የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ የቱሪዝም አገልግሎት የሚሰጥባቸው የመሰረተ ልማት ተቋማት እንዲሁም አስጎብኚዎች ቋንቋን ጨምሮ ያላቸው ሙያዊ የእውቀት እየተሻሻለ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ ይሄም በቀጣይ እንዲዳብር አሳስዋል።
እንደ ዓለም ቱሪዝም ድርጀት መረጃ በኮቪድ ምክንያት በእጂጉ የተቀዛቀዘውን የዓለም የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ ከሁለት እስከ አራት ዓመት ጊዜ ሊፈጅ ይችላል።