በጎንደር ከተማ በአፄ ፋሲል ግቢ የንጉስ እራት ግብዣ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ በአፄ ፋሲል ግቢ የንጉስ እራት ግብዣ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ

ጎንደር ጥር 12/2013 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ በጥምቀት በዓል ለተሳተፉ እንግዶች የክብር መገለጫ የሆነ የንጉስ እራት ግብዣ ሥነ-ሥርዓት ትናንት ምሽት በአፄ ፋሲል ግቢ ተካሄደ።
በሥነ-ሥርዓቱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች ተካፍለዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በወቅቱ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት የንጉስ እራት ግብዣው የጎንደርን ህዝብ አክብረው በጥምቀቱ ለታደሙ እንግዶች የክብር መገለጫ ነው።
የንጉስ እራት በአፄዎቹ ዘመን ነገሳስቱ የጭቃ ሹማምንቶች ባላባቶችን ጠርቶ ግብር የሚጥሉበትና ሹማምንቶቹ ደግሞ ነገስታቱን የሚያመሰግኑበት ሥነ-ሥርዓት እንደነበር አስታውሰዋል።
ነገስታቱ በዓመት በዓል ወቅትና ማግስት ለሹማምንቶች የሚደረግ የተለመደ የእራት ግብዣ መሆኑን ተናግረዋል።
የጥምቀትን በዓል ለማክበር የመጡ የክብር እንግዶችን የንጉስ እራት ግብዣ በአፄ ፋሲል ግቢ መዘጋጀቱን አመልክተው ይህም የቀድሞውን ይዘት የጠበቀ የማዕድ ሥነ-ሥርዓት መሆኑን ገልጸዋል።
የንጉስ እራት ግብዣ የጎንደር ህዝብ አክብረው በጥምቀት በዓሉ ለታደሙ ታላላቅ እንግዶች ክብር ለመግለፅና ለማመስገን የተዘጋጀ እንደሆነም አብራርተዋል።
በቀጣይ በሚከናወኑ ሁለንተናዊ ስራዎች የበለጠ መቀራረብ ለመፍጠር፣ ለመወዳጀትና ለሚከናወኑ የጋራ ሥራዎች ቃል ለመገባባት የታሰበ ነው ብለዋል።
የተዘጋጀው የንጉስ እራት ግብዣ ዓላማውን ያሳከ መሆኑን አቶ ሞላ አስታውቀዋል።
ከንቲባው በህዝብ ዘንድ በታላቅ ጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የጎንደር ጥምቀት በሠላም እንዲከበር መላ ህዝቡ ጠንካራ ትብብር ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በተለይም ወጣቱ በጎንደር ከተማ ከከተራ ጀምሮ የጥምቀት በዓሉ በሠላም እንዲከበር ብርቱ ጥረት ማደረጉን ተናግረዋል።
በዓሉን ለማክበር የመጡ እንግዶችን በትህትና ተቀብሎ ከማስተናገድ ጀምሮ ሥነ -ሥርዓቱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል።
በጥምቀት በዓል በሠላም ተከብሮ እንዲውል መደረጉም በቀጣይ በአባቢው ባለሃብቶችን በመሳብ ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ መጨመር የጎላ ድርሻ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።
የጥምቀት በዓሉ በሠላምና ድምቀት እንዲከበር ላደረጉ ለመላው የጎንደር ህዝብ፣ በተለይም ወጣቶች፣ የፀጥታ አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከንቲባው ምስጋና አቅርበዋል።
በንጉስ እራት ግብዣ ሥነ-ሥርዓት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ፣የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅ ሰሙ ማሞ፣ አርቲስቶች፣ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች፣ ሃይማኖት አባቶችና ሃገር ሽማግሌዎች ተካፍለዋል።