ምዕመኑ የጥምቀት በዓል እሴትና ባህልን ልክ እንደ አይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል - የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን

አዲስ አበባ፣ ጥር 11/2013 (ኢዜአ)  ምዕመኑ የጥምቀት በዓል እሴትና ባህልን ልክ እንደ አይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል ሲሉ በኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ጅቡቲ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ገለጹ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የጥምቀት በዓል ዛሬ በደማቅ ስነ ስርአት ተከብሯል።

በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በተካሄደው የበዓሉ ስነ ስርዓት ላይ የታደሙትን ብፁዕ አቡነ ዳንኤልን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ጥምቀት (ኤፒፋኒ) ኤፒፋኒያ ከሚለው የግሪክ ቃል እንደመጣና ትርጓሜውም የኢየሱስ ክርስቶስ ስጋ መልበስ መምጣትና በዮርዳኖስ ወንዝ በቅዱስ ዮሐንስ መጠመቁን የሚያሳይ ነው።

የኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ የሰው ልጅ ከሃጥያት እንዲድን ምክንያት እንደሆነም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያና በግሪክ ያለው የጥምቀት በዓል አከባበር ተመሳሳይ እንደሆነና በሁለቱም አገሮች ሃይማኖታዊ ስርዓት ውሃው ተባርኮ ሕዝቡ እንደሚጠመቅ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ዳንኤል፤ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ ወንዝና የኢየሱስ ክርስቶስ በረከት የሚገኝበት መሆኑን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያም የጥምቀት በዓል አከባበር በጣም ደማቅ መሆኑንና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የበዓሉን አከባበር ለመታደምና ለመመልከት እንደሚሹ ገልጸዋል።

"በዓሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በታሪክና በሃይማኖት ያላትን ሀብት የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

"ምዕመኑ የጥምቀት በዓል እሴትና ባህልን ልክ እንደ አይኑን ብሌን ሊጠብቀው ይገባል" ያሉት ብፁዕ አቡነ ዳንኤል፤ በተለይም ወጣቱ በዓሉ ይዘቱን ሳይለቅ ዘመናትን የማሻገር ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት ለክፍለ ዘመናት የዘለቀ የእህትማማችነት ግንኙነት እንዳላቸው ብፁዕነታቸው አውስተዋል።

ለአብነትም በአዲስ አበባ ፒያሳ ያለውን ግዙፍ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን አንስተዋል።

የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ይህን ታሪካዊ ትስስር ይበልጥ ለማጎልበት እንዲሁም የሁለቱ አገራት ህዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሰራ ጠቁመዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም