የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ውድድር የመጀመሪያ ድሉን አስመዘገበ

52
አዲስ አበባ ሀምሌ 17/2010 በሩዋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው ሶስተኛው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ውድድር የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አዘጋጇን ሩዋንዳን 3ለ0 በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሉን አጣጥሟል። ሐምሌ 12 ቀን 2010 ዓ.ም የተጀመረው ውድድር ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን ይዟል። ትናንት በስታድ ደ ኪጋሊ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመሰሉ አበራ፣ ምርቃት ፈለቀና ሴናፍ ዋቁማ ጎሎች የሩዋንዳ አቻውን ማሸነፍ ችሏል። ሉሲዎቹ ጨዋታውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ወደ ዋንጫው ፉክክር የተመለሱ ሲሆን ሶስት ነጥብና ሁለት የግብ ክፍያ በመያዝ ከነበሩበት አምስተኛ ደረጃ ወደ ሶስተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችለዋል። ሉሲዎቹ በመጀመሪያ ጨዋታቸው ከኡጋንዳ አቻቸው ጋር ባደረጉት ጨዋታ ሁለት ለአንድ መሸነፋቸው የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ቀጣይ ጨዋታውን ነገ በስታድ ደ ኪጋሊ ነገ ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ያደርጋል። ትናንት በተደረገ ሌላ ጨዋታ ታንዛኒያ ኡጋንዳን 4 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችላለች። በዚሁ መሰረት ታንዛንያ ነጥቧን ወደ አራት ከፍ በማድረግ ወደ ሁለተኛ ደረጃ መምጣት ችላለች። ኡጋንዳ በስድስት ነጥብ የመሪነቱን ደረጃ የያዘች ሲሆን ቀጣይ ጨዋታዋን ነገ ከቀኑ 11 ሰአት ከ15 ደቂቃ ከአዘጋጇ ሩዋንዳ ጋር ታደርጋለች። በአጠቃላይ አምስቱ አገሮች እርስ በእርስ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የተሻለ ነጥብ ያስመዘገበ ቡድን የውድድሩ አሸናፊ ይሆናል። ውድድሩ እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም