በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እየቀረበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እየቀረበ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 11/2013(ኢዜአ) የህግ ማስከበር ሂደት ከተጠናቀቀ ወዲህ ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችና የህክምና አቅርቦቶችን የያዘ የሰብዓዊ ድጋፍ በትግራይ ክልል ለሚገኙ 1.8 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ደርሷል።
በክልሉ 2.5 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም የሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል።
በአስቸካይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል(ኢ.ሰ.ሰ) የሚኒስትሮች ኮሚቴ መሪነት አፋጣኝ ፊላጎቶችን ለማሟላት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከክልል ቢሮዎች፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅቶችና ከዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ የቴክኒክ ቡድኖችን ያካተተ የአስቸኳይ ጊዜ ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ ማዕከል( ኢ.ኦ.ሰ) በመቀሌ ከተማ መቋቋሙን ሰላም ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
ተጨማሪ ፊላጎቶችን ለመለየት ባለ አራት ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበር ስርዓት (የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የምግብ ማከፋፈያ ቦታዎቸን ያካተተ)ተደራጅቶ ወደ ሥራ መገባቱም ታውቋል።
ተለይተው ለታወቁ ተጠቃሚዎች የድጋፍ ሽፋን ለማድረግ እንዲሁም በፍጥነት አቅርቦትን ለማዳረስ የኢትዮጵያ መንግስት ከልማትና ሰብዓዊ አጋሮች ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ መሆኑን ሚኒስቴሩ በመግለጫው ጠቅሷል።
ብሔራዊ የመከላከያ ሰራዊት ደህንነቱ የተጠበቀ የሰዎችና የአቅርቦቶች እንቅስቃሴን በማመቻቸት የሰብዓዊ እርዳታውን ቅንጅት በከፍተኛ ደረጃ በመደገፍ ላይ እንደሚገኝም ተጠቅሷል።
ስርጭቱ በብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ በአለም አቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ (ዩ.ኤን.ኦቻ) አስተባባሪነት በዓለም አቀፍና በሀገር በቀል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በሰፍትኔት መርሃ ግብር (ፒ.ኤስ.ኤን.ፒ) እየተከናወነ መሆኑንም መግለጫው ያትታል።
ስርጭቱ የሚከናወነው በአክሱም፣ አዲግራት፣ አላማጣ ፣ መቀሌ ዙሪያ፣ ሽሬና መቀሌ ከሚገኙ የማሰራጫ ጣቢያዎች እንደሆነም ነው የተገለጸው።
በስርጭት ሂደቱ ለሴቶች፣ ህጻናት፣ አረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች ለምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስና የህክምና አቅርቦቶች ስርጭት ቅድሚያ እየተሰጠ ይገኛል ተብሏል።
መንግስትና ሰብዓዊ አጋሮች እ.ኤ.አ. ህዳር 29 ቀን 2020 በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሰረት በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ የጠቀሰው መገለጫው፤ የተጠቃሚዎችን ብዛት በትክክል ለመለየት የጋራ የፊላጎት ዳሰሳና ግምገማ በማካሄድ ላይ እንደሆኑም ተገልጿል።
ለዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማዳረስ ትኩረት ተሰጥቶ በቁርጠኝነት ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም የሚኒስቴሩ መግለጫ ያሳያል።