ቀጥታ፡

ወጣቶች በሐይማኖታቸው ላይ የሚያሳዩትን ህብረትና አንድነት በአገራዊ አንድነት ላይም እንዲያውሉት ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 11/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በሐይማኖታቸው ላይ የሚያሳዩትን ህብረትና አንድነት በአገራዊ ሰላምና አንድነት ላይም እንዲያውሉት ተጠየቀ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ከዘጠኙ አበይት በአላት መካከል አንዱ የሆነውና በብዙ ሺዎች በአደባባይ ደምቆ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ዘንድሮም እንደወትሮው ሁሉ በደማቅ ስነ-ስርአት ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያሪክ ብጹዕ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ብፁዓን አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችና ሌሎችም እንግዶች በታደሙበት ተከብሯል።

ታቦታትም በካህናቱ አኮቴት (ምስጋና) እና ሽብሸባ፣ በሰንበት ተማሪዎች ያሬዳዊ ዜማ፣ በበርካታ ምዕመናኖች  በእልልታና በሆታ ታጅበው ወደየ አድባራቶቻቸው ተሸኝተዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በዓሉን ለመታደም የተገኙ እና ቦታውን ከማጽዳት ጀምሮ በተለያዩ በጎ ስራዎች ላይ ተሳታፊ የነበሩ ወጣቶች ለበአሉ ከማጽዳት ምንጣፍ ከመዘርጋትና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ስራ በመስራት ሐይማኖታዊ ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።

በተለይም ጃንሜዳን በማጽዳት በተከናወነው ስራ ላይ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ የሙስሊም እና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችም ጭምር ተሳታፊ እንደነበሩ ተናግረዋል።

በዚህም ወጣቱ በተባበረ ክንድ በአንድነት ከተጋገዘ ኢትዮጵያን ወደ ፊት ሊያስቀጥሉ የሚችሉ የጋራ አገራዊ ስራዎችን መስራት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።

ለእምነቱ የሚታዘዝ እና የሚተባበር ብሎም በጋራ ለአንድ አላማ የሚቆም ወጣት ሰላም ከሌለ አገርም ሆነ ህዝብ እንደማይኖር በመገንዘብ አብሮነቱን በማጠናከር ሰላምን ማስፈን እንደሚገባውም ተናግረዋል።

በመሆኑም ህዝቡ በሐይማኖቱ ላይ የሚያሳየውን ህብረትና አብሮነት በአገራዊ ሰላምና አንድነት ላይም ሊያውለው ይገባልም ነው ያሉት።  

መንግስትም ይህንን የአገር ምሶሶ የሆነውን የወጣት ሃይል በፍቅርና በአንድነት በማስተሳሰርና በመሰብሰብ በበጎ አላማ ሊጠቀምበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች መካከል አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም