ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል የፍቅር፣ ምህረት፣ ሠላምና ይቅርታ ተልእኮን የምንወጣበት ዕለት ነው- የካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፣ ጥር 11/2013 (ኢዜአ)  የጥምቀት በዓል ፍቅር፣ ምህረት፣ ሠላምና ይቅርታን የመስበክ ተልእኮ የሰጠንን አምላክ እያመሰገንን ክርስትያናዊ ተልእኳችንን የምንወጣበት ዕለት ነው ሲሉ የካቶሊካዊት ቤተክርስትያን አባቶች ተናገሩ።

ጥምቅት ኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናንና ፍቅርን ያስተማረበት በዓል በመሆኑ ምዕመናን እርስ በርስ በመዋደድና በመደጋገፍ ሊያከብሩት ይገባልም ብለዋል። 

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የቅዱስ ፍራንችስኮስ ገዳም የጥምቀት በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ዛሬ ተከብሯል።

በቅዳሴ፣ በወጣቶችና ምዕመናን ዝማሬ የተደረገ የጥምቀት ስርዓቱ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ጠቅላይ ፅህፈት ቤት የሐዋርያዊ መምሪያ ኃላፊ አባ ገብርኤል ወልደሃና በእለቱ ባደረጉት ንግግር ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ በባህረ ዮርዳኖስ በዮሃንስ እጅ ተጠምቆ ፍቅሩንና ትህትናውን የገለፀበት በዓል ነው ብለዋል።

ጥምቀት ምስጢረ ስላሴ  እንዲሁም የወልደ እግዚአብሄር ልጅነት የተገለፀበት የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ስራ ለዓለም በይፋ የታወጀበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በካቶሊክ ቤተክርስትያን ሥርዓት ገና ወደ ቤተክርስትያን ስንገባ የቀኝ እጃችንን ጣቶች መግቢያ ላይ በሚገኘው ጸበል ራሳችንን እንባርካለን፤ ይህም ቡራኬ ጥምቀታችንን ያስታውሰናል በጥምቀትም የሰማይ ወራሾች መሆናችንን እናስባለን ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ካቶሊካዊት ሰበካ የሐዋሪያ አገልግሎት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አባ ጴጥሮስ በርጋ ናቸው።

የዘንድሮው ጥምቀት አገሪቱ በሰላምና በኮሮና ወረርሽኝ ላይ ሆና እያከበረችው መሆኗ ለየት እንደሚያደርገው አባቶቹ ተናግረዋል።

ምዕመናን በዓሉ ሲያከብሩ በመተሳሰብና ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማሩትን ትህትና በክርስትናቸው በተግባር በመግለፅ ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል።

በበዓሉ ላይ ያነጋገርናቸው ምዕመናንም የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር በተግባር የገለፀ ህይወት መኖር እንደሚገባ አስረድተዋል።

በዓለም ዙርያ የሚገኙ ክርስትያኖች 54ኛውን የክርስትያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ትላንትና መጀመሩንና እስከ ጥር 17 ዓ.ም የሚቆይ መሆኑም ተገልጿል።

የጸሎት ሳምንቱ ክርስትያኖች በቤተክርስትያን መካከል የመቀራረብ፣ የዕርቅ እና የአንድነት መንፈስ እንዲሰፍን ጸሎት የሚያደርጉበት መሆኑም ተመላክቷል።

በኢትዮጵያ የፀሎት መርሃግብሩ ማጠናቀቂያ የፊታችን እሑድ ጥር 16 ቀን 2013 ዓ.ም የሁሉም አብያተክርስትያናት መሪዎች በአንድ ላይ በካቶሊክ ቤተክርስትያን አስነሳሽነት በጋራ የጸሎት መርሐግብር ስለ ክርስትያኖች አንድነትና መልእክት በማሰተላለፍ ይጠናቀቃልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም