አመታዊ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል በመንዝ ጌራ ወረዳ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

70

ደብረብርሀን፣ ጥር 11/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ቀናት ሲካሄድ የቆየው 18ኛው ዓመታዊ የባሕል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል በመንዝ ጌራ ወረዳ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

በመንዝ ማማ ምድር ወረዳ በሞላሌ ከተማ በተካሄደው ውድድር ከ24 የገጠር ወረዳዎችና ከስድስት የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ670 በላይ ስፖርተኞች ተሳትፈዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃድቅ ለአሸናፊዎች ዋንጫና ለተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት ከሰጡ በኋላ እንደገለጹት የባህል ስፖርትን ማሳደግና ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ማስረከብ ያስፈልጋል።

ውድድሩ ከየወረዳው የሚመጡ ወጣቶችን እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ ከማድረግ ባለፈ በየአካባቢዉ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን ለማስተዋወቅና ዘርፉን ለማልማት ፋይዳዉ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የስፖርት ዘርፉ አንድነታችንን እንድናጠናክርና ዘመን ተሻጋሪ ታሪኮችን ጠብቀን ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ ጠቃሚ በመሆኑ ሁሉም ሊጠብቀውና ሊንከባከበው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዞኑ ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃን ጨርቆስ በበኩላቸው በገበጣ፣ ፈረስ ጉግስ፣ ትግል፣ ፈረስ ሸርጥና የገና ጨዋታን ጨምሮ በዘጠኝ የባህል ስፖርት አይነቶች ውድድሩ መካሄዱን ተናግረዋል።

በውድድሩ የመንዝ ጌራ ወረዳ በአጠቃላይ ውጤት አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን የባሶና ወራናና የወደራ ወረዳዎች በቅደም ተከተል 2ኛና 3ኛ በመሆን የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።

በመጪው የካቲት ወር በክልል ደረጃ በኮምቦልቻ ከተማ በሚካሄደው ክልል አቀፍ የባህል ስፖርት ውድድር ዞኑን ወክለው የሚሳተፉ 45 ስፖርተኞች መለየታቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል።

ከተለያዩ ወረዳዎች የመጡ ተወዳዳሪዎችም የአለባበስ፣ የአመጋገብና ባህላዊ የአጨዋወት እንዲሁም ጭፈራዎችን በፌስትባሉ በማቅረብ ባህላቸውን አስተዋውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም