ቀጥታ፡

የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ለሽሬ እና አካባቢው ነዋሪዎች አልሚ ምግብና መድሃኒት ላከ

ጥር 10/2013 (ኢዜአ) የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ለሽሬ እና አካባቢው ነዋሪዎች 500 ኩንታል አልሚ ምግብና መድሃኒት ድጋፍ ወደ ስፍራው ላከ፡፡

ኮሚሽኑ አልሚ ምግቦቹ እና መድሃኒቶቹ በፍጥነት ወደ ስፍራው እንዲደርሱ በማሰብ  በኢፌዴሪ አየር ሃይል እቃ ጫኝ አውሮፕላን አጓጉዟል፡፡

የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሣ፤ ቁሳቁሱ ወደ ስፍራው በተላከበት ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ ችግር ለገጠማቸው ዜጎች ድጋፍ  የማድረስ ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡  

ከዚህ ቀደም ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል መቀሌን ማዕከል በማድረግ ለሁሉም አከባቢዎች  እርዳታ ማድረሱንም አስታውሰዋል።

በዛሬው ዕለትም ለህጻናት እና እናቶች የሚውል 500 ኩንታል አልሚ  ምግብ  ለሸሬ  እና  አከባቢዋ ነዋሪዎች መላኩን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከ2 ሚልየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ መድሃኒቶች ወደ  ስፍራው  መላኩንም ኮሚሽነር ምትኩ ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል እስካሁን በኮሚሽኑ በኩል ለ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍና እርዳታ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

እርዳታው በተለይ ከተሞች አካባቢ በህግ ማስከበር ሂደቱ ገቢያቸው ለተቋረጠባቸው ወገኞች እና በገጠርም አካባቢ ላሉት ነዋሪዎች መድረሱን አመልክተዋል፡፡

በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በሀገሪቱ ሌሎች እርዳታ ለሚሹ ወገኖች የሚውል 20 ሺህ ሜትሪክ ቆን  እህል ከውጭ  እየገባ መሆኑነም ጠቅሰዋል።

የእርዳታ እህሉ ጅቡቲ ወደብ መድረሱን የገለጹት ኮሚሽነር ምትኩ በአሁኑ ጊዜ በቀን  ከ15 እስከ 20 ሺህ ኩንታል ወደ ሀገር ውስጥ እየተጓጓዘ ይገኛል ብለዋል፡፡

የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በሀገሪቱ በተለያዩ ሁኔታዎች ጉዳት ደርሶባቸው እርዳታ ለሚያሥፈላጋቸው ወገኞች ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም