ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት 65ተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የፊታችን ሀሙስ ያከብራል

ጥር 10/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት 65ተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የፊታችን ሀሙስ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከበር አስታወቀ። በበዓሉ አርመናዊዩ ሙሴ ነርሲስ ናልባንዲያን ጨምሮ በቴአትርና በሙዚቃ ዘርፍ የጎላ አስተዋጾ የነበራቸው ግለሰቦች እንደሚታሰቡም ተገልጿል።

የበዓሉን አከባበር በሚመለከት በዛሬው እለት ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

የክብረ በዓሉ ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አዳፍሬ ብዙነህ እንደገለጹት በዓሉ ሲከበር በሁለት ዘርፍ ከአንጋፋዎቹ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ውስጥ በመምረጥ ለመዘከር መታሰቡን አመልክተዋል።

በዚህም በቴአትር ዘርፍ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን፣ ገጣሚ እና ጸሐፊ ተውኔት መንግሥቱ ለማ እና በኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትርን ያስተዋወቀው አባተ መኩሪያን ለመዘከር መታሰቡን ተናግረዋል።

"በሙዚቃ ዘርፍ ደግሞ ሙዚቀኛ መራዊ ስጦት እና ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ መዳበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት አርመናዊው ሙሴ ነርሲስ ናልባንዲያን ይታሰባሉ" ብለዋል።

በሙዚቃና በቴአትር የተለያዩ ዝግጅቶች የሚቀርቡ ሲሆንና ከእነዚህ ወስጥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት ክፍል ተዘጋጅተው የሚመጡ ቴአትሮች ይገኙበታል ተብሏል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርን በሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ የነበሩ ኃላፊዎች እና ከቴአትር ቤቱ በጡረታ የተገለሉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በዝግጅቱ የሚታደሙ ሲሆን የምስጋና ዝግጅትም የሚደረግላቸው መሆኑ ታውቋል።

በበዓሉ ላይ በሀገሪቱ ከሚገኙና የቴአትርና የሙዚቃ የትምህርት ክፍል ካላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ተጋባዥ እንግዶች እንደሚገኙም ነው  አቶ አዳፍሬ የተናገሩት።

በዓሉ ኮቪድ-19ን ለመከላከል የወጣ መመሪያን ተግባራዊ ባደረገ መልኩ እንደሚከበርና 300 ሰዎች ብቻ የሚታደሙበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትጵያ ብሔራዊ ቴአትር ህዳር 3 ቀን1948 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተመርቆ ሥራውን የጀመረ አንጋፋ ቴአትር ቤት መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም