በምዕራብ ኦሮሚያ የጥምቀት በዓል በሠላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ኦሮሚያ የጥምቀት በዓል በሠላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ
ጥር፤ 10/2013 ነቀምቴ (ኢዜአ) በምዕራብ ኦሮሚያ ነቀምቴ ከተማ ፣ ምስራቅ፣ ምዕራብ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች የጥምቀት በዓል በሠላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ።
የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የአካባቢ ሠላም ማረጋገጥ የሥራ ሂደት አስተባባሪ ኢንስፔክተር ከበደ ኤጀርሶ ለኢዜአ እንዳሉት በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ሀይሉ በመቀናጀት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት አድርጓል፡፡
በአስተዳደሩ ታቦታቱ በሚያልፉባቸው ቦታዎች የመደበኛ ፖሊስና ኦሮሚያ ፖሊስ ልዩ ኃይል አባላት ተሰማርተው በዓሉ በሠላም እንዲከበር ጥበቃ እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የምሥራቅ ወለጋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ታሪኩ ድርበባ በበኩላቸው የጥምቀት በዓል በሚከበርባቸው በዞኑ 17 ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር ፀጥታ አስከባሪዎችን ከዋዜማው ጀምሮ በመመደብ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት በዓል ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ በዞኑ 20 ወረዳዎችና ሶስት የከተማ አስተዳደሮች ከሃይማኖት አባቶች፣ ሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁን የገለጹት ደግሞ የምዕራብ ወለጋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ተመስጌን ቶሌራ ናቸው፡፡
በአካባቢዎቹ የጸጥታ አካላት ተመድበው ህግና ሥነ-ሥርዓት እያስከበሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በተመሳሳይ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር የጥምቀት በዓሉ በሠላም እንዲከበር ታቦታቱ በሚያልፉባቸው አካባቢዎች የፀጥታ አካላት ተመድበው ቋሚና ተንቀሳቃሽ ጥበቃ እያደረጉ መሆናቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽንና ሚዲያ ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ወንድሙ ዋቅወያ አስታውቀዋል፡፡
ለበዓሉ ስኬት ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር መተባበር እንዳለበት አመልክተው በበዓሉ ሂደት ሊፈጠሩ ከሚችሉ ስርቆት፣ ሀሰተኛ የብር ኖት ዝውውርና ድንገተኛ የእሳት አደጋ ራሱን መጠበቅ እንዳለበት አመልክተው ችግር ሲያጋጥመው ፈጥኖ ለፖሊስ እንዲያሳውቅም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡