የጥምቀት በዓል ትውልዱ ለባህላዊ አልባሳት ትኩረት እንዲሰጥ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ... አስተያየት ሰጪዎች

ጎንደር፤ ጥር 10/2013(ኢዜአ) በጥምቀት በዓል በተለያዩ ንድፎች ተዘጋጅተው ለሽያጭ የሚቀርቡ የባህል አልባሳት ምርቶች ትውልዱ ለባህላዊ አልባሳት ትኩረት እንዲሰጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በጎንደር ከተማ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ፡፡

ተጠቃሚዎችና ነጋዴዎች ለኢዜአ እንዳሉት የከተማዋ ነዋሪዎች  የጥምቀት በዓልን  ምክንያት በማድረግ ባህላዊ እሴቱን ሳይለቅ የተዘጋጁ የባህል አልባሳትን በተመጣጣኝ  ዋጋ እየገዙ ነው።

ወጣት መኳንንት ሲሳይ በሰጠው አስተያየት ዘመኑን በሚመጥንና በሁሉም የእድሜ ደረጃ ተዘጋጅተው የሚሸጡ የባህል አልባሳት ወጣቱ በሀገሩ የባህል አልባሳት እንዲኮራና  እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጿል፡፡

"ሴት ልጅ አምራና ደምቃ የምትታይበት እለት ቢኖር ጥምቀት ነው" ያሉት ደግሞ  ወይዘሮ  እቴናት ሞላ ናቸው።

ከፊትና ኋላው በመስቀል ቅርጽ ተጠልፎ የሚዘጋጀው የጎንደር የባህል ቀሚስ በበዓሉ  ተፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ጀምበሩ አይሸሹም በበኩላቸው "የቀደምት አባቶቻችን የጀግንነትና የተጋድሎ ተምሳሌታዊ አለባበስ የሆነው የጃኖ ባህላዊ ልብስ ለጥምቀት በዓል የባህል ማድመቂያ ከሆኑ  ባህላዊ አልባሳት አንዱ ነው" ብለዋል፡፡

ትውልዱ ባህሉ፣ እምነቱንና የቀደምት አባቶቹን የአለባበስ ሥርዓት  ጠብቆ በማቆየት  ረገድ ጥምቀትን የመሳሰሉ በዓላት  የጎላ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

"የወጣቱን፣ የጎልማሳውን ፣የአዛውንቱንና የወይዛዝርቱን የአለባበስ ሥርዓት ጠብቀው የሚዘጋጁ የባህል አልባሳት ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓይነትም ብዛትም እየጨመሩ መጥተዋል" ያሉት ደግሞ የባህል አልባሳት ነጋዴ ወይዘሮ ፋጤ ያሲን ናቸው፡፡

በጎንደር አካባቢ በስፋት የሚዘወተረው የጎንደር የባህል ቀሚስ በዘንድሮ የጥምቀት በዓል ተፈላጊነቱ መጨመሩንና እስከ 1ሺ 200 ብር እየተሸጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሌላው የባህል አልባሳት ነጋዴ አቶ ሲራጅ መሐመድ በበኩላቸው በወርሃ ጥር፤ ጥምቀት ብቻ ሳይሆን ጋብቻ ፈጻሚ ጥንዶችም የባህል አልባሳት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከ2ሺ ብር ጀምሮ እስከ 8ሺ ብር የሚሸጥ የባህል አልባሳት መኖሩን ጠቁመው፤ ጥምቀት ላይ የሚታደሙና ሙሽሮችም ምርቶቻቸውን በስፋት እየገዙዋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጥምቀት በዓል በጎንደር በታላቅ ሃይማኖታዊ  ሥርዓት ከዋዜማው ጀምሮ በድምቀት በመከበር ላይ እንደሚገኝ ሪፖርተራችን ከሥፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም