የዘመን ድራማ ተሳታፊ አርቲስቶች በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የበጎ አድራጎት ስራ ሰሩ

67
አዲስ አበባ ሀምሌ 16/2010 የዘመን ድራማ ተሳታፊ አርቲስቶች በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመገኘት  የበጎ አድራጎት ስራ አከናወኑ። አርቲስቶች የበጎ አድራጎት ስራ ያከናወኑት መደመርን በተግባር ለማሳየትና ጥቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያስተላለፉት የመተባበርና የአንድነት መርህ ለመደገፍ ያለመ ነው። የዘመን ድራማ ዳይሬክተር አርቲስት ሰለሞን ዓለሙ  እንደገለጸው፤ የበጎ አድራጎት ተግባር ወር በገባ በ16ኛው ቀን ለማከናወን ወስነዋል። አርቲስቶች ዛሬ ባደረጉት  የበጎ አድራጎት ስራ ህሙማንን የማጽናናት፣ የመንከባከብና መድሃኒቶቸን ከቦታ ቦታ የማንቀሳቀስ ስራ ሰርተዋል። ይህ በጎ ተግባር በቀጣይ በሌሎች ዘርፎች ላይ እንደሚቀጥል አርቲስት ሰለሞን ጠቁሟል። በበጎ አድራጎት የተሳተፉት ሌሎች አርቲስቶች በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የበጎ አድራጎት ተግባር በአርቲስቶች ብቻ ሳይሆን በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች መለመድ አለበት። አርቲስት ቅድስት ጀቴ በሰጠችው አስተያየት˝ እነሱን ድኖ መውጣት እንደሚችሉ መንገር እነሱን መርዳት  አስታማሚዎች ራሳቸው ይደክማሉ  እነሱን ማስታመም መድሃኒት መስጠት ብዙ ነገር አለ፤ በተቻለን አቅም በወር ውስጥ በ16 ስምንት ሰዓት ሰጥተን እነሱን መርዳት ብንችል˝ ነው ያለው። ˝ወገኖቻችን ታመው ያሉ እነሱን ለማጽናናትና ለማገዝ የሚገባን ነገር ካለ በጉልበታችን በማገዝ አረአያ ለመሆን ነው ፍቅራችን ማህበራዊ ትስስራችን ወደ ነበረበት ለመመለስ ኢትዮጵያዊነትን መደመር ከሚለው ጋር ይሄዳል˝በማለት የገለጹት አቶ ሀይለኪሮስ ታደሰ ናቸው። የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ  ሆስፒታል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ አምዴ በበኩላቸው የዘመን ድራማ አርቲስቶች የጀመሩት በጎ ተግባር ሌላውን ህብረተሰብ የሚያነሳሳና የበጎ አድራጎት ተግባርን የሚጨምር ጅምር እንደሆነ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም