የጥምቀት በዓል ትሩፋቶች

በመንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)

ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ በርካታ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ያላት አገር ነች። እነዚህ በዓላት በሀገሪቱ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝተው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገቡት አስራ ሁለት ደርሰዋል። ይህም ሀገሪቱ ባስመዘገበቻቸው ቅርሶች ከአፍሪካ ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ እንድትሰለፍ አስችሏታል።

በዩኔስኮ ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል የጥምቀት በዓል አንዱ ነው። የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ታህሳስ 01 ቀን 2012 ዓ.ም ሲሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን በድምቀት ይከበራል። በዓሉ በየዓመቱ የሚከበረው ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ ጥር 11 ቀን 31 ዓ.ም. (በ5531 ዓ.ዓ) በአጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት ለማስታወስ እንደሆነ የቤተ ክርስቲያኒቷ ሊቃውንት ያስረዳሉ።

የጥምቀት በዓል በብሔራዊ ደረጃ መከበር የጀመረው በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነገሥታቱ አብርሃና አጽብሐ የክርስትና ሃይማኖትን ተቀብለው ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን ማድረጋቸውን ተከትሎ መሆኑን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ሰነዶች ያመለክታሉ። የጥምቀት በዓል በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚከበር ቢሆንም በተለይ በአክሱም፣ በላልይበላና በጎንደር በአፄ ፋሲል መዋኛ እንዲሁም በአዲስ አበባ በተዘጋጀላቸው የክብር ቦታ ህዝበ ክርስቲያኑ ከተለያዩ ሀገራት ከሚመጡ ቱሪስቶች ጋር በባህላዊ አለባበስ በደመቀ ሁኔታ የሚከበር መሆኑ ልዩ ያደርገዋል። “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” በሚል የሀገራችን ብሂልም ይታወቃል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዳይሬክተር ዶ/ር አበባው ይርጋ “የጥምቀት በዓል ምንነቱ፣ ማሕበረ-ባህላዊ አውዶቹና ፋይዳዎቹ” በሚል ርእስ ባካሄዱት የጥናት ሰነዳቸው ላይ እንደጠቀሱት የጥምቀት በዓል አከባበር ሀይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ባህላዊም ይዘት ያለው በመሆኑ በርካታ ማህበራዊ ጠቀሜታዎች አሉት። በጥናት ሰነዱ ላይ እንደተመለከተው በማህበራዊ ጠቀሜታነት ከሚቀርቡ ማህበረ-ባህላዊ ክንዋኔዎች መካከል በበዓሉ አክባሪዎችና ተሳታፊዎች የሚቀርቡ የተለያዩ ባህላዊ ዘፈኖች አንዱ ነው። ይህም ከልብ የመነጨ ደስታን የሚገልጹበትና ማህበራዊ መስተጋብራቸውን የሚያጠናክሩበት ከማህበረሰቡ ባህል ጋር እጅግ የተጣመሩ መሆናቸውን የሚያሳዩበት ነው።  ሌላኛው ማህበራዊ ገጽታ ከጥቃቅን እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚደርስ የንግድ ልውውጥ የሚካሄድበት ሂደት ሲሆን በዚህም ከሱቅ በደረቴ እስከ ባዛርና አውደ ርእይ ዝግጅት የደረሰ የንግድ ክንዋኔዎችን ያጠቃልላል። የጥምቀት በዓል ወጣቶች ለመተጫጨት የሚጠቀሙበት ሲሆን በዚህ ዕለት ወንዶች እንደሌላው ጊዜ ስለሚያጯት ሴት ዘር ምንነት ብዙም እንደማይጨነቁ ዶ/ር አበባው በጥናታቸው አመልክተዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝምና ሆቴል የትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ አያና ፍስሐ እንደሚገልጹት የጥምቀት በዓል በዓለም የማይዳሰሱ የሰው ልጆች ቅርስነት መመዝገቡ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። የጥምቀት በዓል የበርካታ ቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ የሚታወቅ ሃይማኖታዊ ሁነቱን እንደጠበቀ የቆየና በዓለም ቅርስነት ከመመዝገቡም ቀደም ብሎ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እያደገ የመጣ ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡ በተጨማሪም “ጥምቀት በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ በዓለም ዙሪያ በስፋት እንዲታወቅ ከትልልቅ ሆቴሎች ጀምሮ እስከ አነስተኛ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የቱሪስቱን ፍሰት እንዲጨምር ያደርጋል” ይላሉ።

የጥምቀት በዓል የኢትዮጰያውያንን ማህበራዊ እሴቶች ከፍ እንዲሉ አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱ ሁነቶች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ይታወቃል። የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ወቅት በየቤቱ የመስተንግዶ ዝግጅት ተደርጎ ወዳጅ ዘመድ ተጠራርቶ አብሮ ይመገባል፤ ይገባበዛል። ጎረቤት ይጠያየቃል፤ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ ይደረጋል። በዓሉ በብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ አለባበስ በመድመቅ ሰላማዊ በሆነ መልኩ የሚከበር ከመሆኑም ባሻገር ክዋኔዎቹ የሀገር ገጽታን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ በኩል ጉልህ ድርሻ አለው።      

የጥምቀት በዓል አከባበር ለማክበርና ስነስርዓቱን ለመመልከት በየዓመቱ በርካታ የተለያዩ ሀገራት ጎብኝዎች፣ ዲፕሎማቶችና አምባሳደሮች ይታደማሉ፡፡ ዘንድሮም በዓሉን በድምቀት ለማክበር በልዩ ሁኔታ ዝግጅት ተደርጓል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት የውጭ ጎብኝዎች ዘንድሮ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ከዚህ ቀደም ሲከበር በነበረው ደረጃ እንደማይገኙ ቢታመንም በተቻለ መጠን የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ከፍተኛ የማስተዋወቅ ስራዎች ቀደም ብለው መጀመራቸውን የበዓሉ አዘጋጆችና አስተባባሪዎች የሚሰጡት መረጃ  ያሳያል፡፡

በዓሉ በተለየ ስርዓትና ድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች መካከል የአዲስ አበባና የጎንደር ከተሞች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡ በዓሉ ሲከበር በርካታ የውጭና የውስጥ ጎብኚዎችና የበዓሉ ተሳታፊዎች እንዲገኙ ለማድረግ በዚህም የየከተሞቹን ቱሪዝም ለማነቃቃትና ከሚገኘው ገቢ አካባቢዎቹን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። በዚህ ዓመት የሚከበረው የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያዊያንን አንድነትና የጎረቤት አገራትን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር የበለጠ በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር የአዲስ አበባና የጎንደር ከተሞችን ጨምሮ የየአካባቢዎቹ የመንግስት ሀላፊዎች፣ የበዓሉ አዘጋጆችና አስተባባሪዎች ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ በርካታ ታቦታትን በአንድ ላይ የሚያሰባስበውና ቀደም ሲል በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የንግድ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ የነበረውን የጃን ሜዳ በከተማ አስተዳደሩና በቤተክርስቲያኗ የጋራ ርብርብ በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሶ ለበዓሉ ዝግጁ ተደርጓል።

በጎንደር ከተማም በዓሉ ቀደም ሲል ይከበርበት ከነበረው ሁኔታ የተለየ ለማድረግ "ኢትዮጵያ እንደገና ጥምቀትን በጎንደር" በሚል መሪ ሃሳብ ከጥር 1 እስከ 12 ያለውን ቀን የጥምቀት በዓል ሳምንት በሚል አውጃ የባህል ትውውቅ፣ የቁንጅና ውድድር፣ የአጼ ቴዎድሮስ የልደት በዓል፣ ባዛር፣ የሙዚቃ ድግሶችና ሌሎች ሁነቶችን ጨምሮ ስታከናውን ቆይታለች፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በዓሉ በተሳካ ሁኔታ እንዲከበር ከፀጥታ ተቋማት፣ ከወጣቶች፣ ከባለሃብቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውን ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል። የዘንድሮው የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያዊያንና የጎረቤት አገራት ሕዝቦችን ትስስር ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር በጎንደር መታቀዱን የከተማው አስተዳደር አስታውቋል።  

የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ገጽታው ባሻገር ማህበራዊ ፋይዳው እጅግ የጎላ ነው። በዓሉ የህዝቦችን አብሮነት የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም ግዙፍ ነው። በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት በዓል ዘንድሮ የሚከበረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የዓለማችን ከፍተኛ ስጋት በሆነበት ወቅት በመሆኑ ለቫይረሱ ከሚያጋልጡ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች በመቆጠብ የጤና ባለሙያዎችን የመከላከያ ፕሮቶኮሎችና ህግጋት ተግባራዊ ባደረገ መልኩ መሆን አለበት መልክዕክታችን ነው።

መልካም በዓል!!!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም