ዩኒቨርሲቲዎች ውይይትና የሃሳብ ሙጉት የሚካሄድባቸው መድረኮች ሊሆኑ ይገባል - ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ

92

ጥር 8 / 2013 (ኢዜአ) ዩኒቨርሲቲዎች ከተቋቋሙበት ዓላማ በተጨማሪ ውይይትና የሃሳብ ሙጉት የሚካሄድባቸው መድረኮችና ተቋማት ሊሆኑ እንደሚገባ ተጠቆመ።

በሠላም ሚኒስቴርና በወራቤ ዩኒቨርሲቲ ትብብር "የሠላም ወግ፤ ብሔራዊ መግባባት ለኢትዮጵያ እድገት" በሚል መሪ ሃሳብ ወራቤ ላይ ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ በሥልጤ ዞን የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የታሪክና የሥነ-ዜጋ መምህራንና የወራቤ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ተሳትፈዋል።

ውይይቱን ያስጀመሩት የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ቶፊክ ጀማል የአገር ሠላም የግለሰብ፣ የማኅበረሰብና የተቋምን ሠላም በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

የውይይቱ ዓላማ ሠላም ለአገር ዕድገትና ብልጽግና ያለውን ፋይዳና ከታሪክ ጋር ያለውን ቁርኝት ማመላከት መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ የሚገኙ አመራሮች ስለ ሠላም ፋይዳ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ታስቦ መዘጋጀቱንም አክለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና እስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰርና የሠላም ሚኒስቴር የፖሊሲ አማካሪ ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ ዩኒቨርሲቲዎች ከትምህርት ሥራቸው በተጨማሪ የውይይትና የሃሳብ ሙጉት የሚደረግባቸው መድረኮች ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ይህ ሳይደረግ በመቆየቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በዩኒቨርሲቲዎች ጭምር ግጭቶችና ችግሮችን ማየት እየተለመደ መምጣቱን አውስተዋል።

"ችግሮችን ለመፍታትና ለመግባባት በሰለጠነ መንገድ መወያየት በቂ ነው" ያሉት ዶክተር ሳሙኤል ይህን ለማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አመልክተዋል።

የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ እና የእስያ ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፈሰር ዶክተር ደቻሳ አበበ "ታሪክ በምናስተምርበት ወቅት የፖለቲካ ታሪክ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ የለብንም" ብለዋል።

በታሪክ የግጭትና የጦርነት ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ መስተጋብሮችና በኢኮሚያዊ ግንኙነቶች ያሉት ጭምር ሊተኮርባቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሌላው ጽሁፍ አቅራቢ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲት ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ተሾመ አበራም "ኢትዮጵያዊነት የእኩልነት፣ የነጻነትና የዴሞክራሲ መፈክር ነው" ብለዋል።

በሠላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት የሚካሄደው "የሠላም ወግ" የምሑራን ውይይት ቀጣይ እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም