በቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ባህር ዳርን ሲያሸንፍ ወላይታ ዲቻ ከሰበታ ከተማ ዜሮ ለዜሮ ተለያየ - ኢዜአ አማርኛ
በቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ባህር ዳርን ሲያሸንፍ ወላይታ ዲቻ ከሰበታ ከተማ ዜሮ ለዜሮ ተለያየ
ጂማ ፤ ጥር 08/2013 (ኡዜአ) በጅማ ከተማ እየተካሄደ ባለው ሰባተኛው የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ቤት ኪንግ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ባህር ዳርን ሲያሸንፍ ወላይታ ዲቻ ከሰበታ ከተማ ዜሮ ለዜሮ ተለያዩ ፡፡
ዛሬ አራት ሰዓት ላይ ባህር ዳርን የገጠመው ሀዋሳ ከተማ ሁለት ለአንድ አሸንፏል።
ከእረፍት በፊት በ21ኛው ደቂቃ የመጀመሪዋን ጎል ስለአምላክ ተገኝ ለባህርዳር ያስቆጠረ ሲሆን መስፍን ታፈሰ ደግሞ በ24ኛው ደቂቃ ለሀዋሳ ከተማ ግብ አስቆጥሯል፡፡
ከእረፍት በኋላ ኤፍሬም አሻሞ በ59ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ግብ ሀዋሳ ከተማ ድል ቀንቶታል፡፡
ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን አስር ያደረሰ ሲሆን ደረጃውንም ወደ አምስት ማሻሻል ችሏል፡፡
ወላይታ ዲቻ ከሰበታ ከተማ ዜሮ ለዜሮ ከመለያየቱ ጋር ተያይዞ ነጥቡን ከሶስት ወደ አራት ማሳደግ ችሏል፡፡
ተጋጣሚው ሰበታ ከተማ ደግሞ ነጥቡን ወደ ስድስት ከፍ አድርጓል፡፡
ሁለቱም ተጋጣሚዎች የደረጃ ለውጥ አላደረጉም፤ ወላይታ 12ኛ ፤ ሰበታ ደግሞ ዘጠነኛ ደረጃቸውን ይዘው ቀጥለዋል፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ትናንት በተጀመረው ሰባተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ቤት ኪንግ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጅማ አባጅፋርን ሶስት ለሁለት ማሸነፉን በወቅቱ ተገልጿል።