ተመራቂዎች ጠባቂ ሳይሆኑ አጋጣሚውን ሁሉ በመጠቀም ሥራ ፈጣሪ መሆን አለባቸው ... አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

118

ደሴ፤ ጥር 8/2013(ኢዜአ) ተመራቂዎች ጠባቂ ሳይሆኑ አጋጣሚውን ሁሉ በመጠቀም ሥራ ፈጥረው ወደ ተግባር መግባት እንዳለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ የትምህርት ፕሮግራም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን ከ800 በላይ ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት  በክብር እንግድነት የተገኙት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዳሉት  ተማሪዎች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ሃገራቸውን ከድህነት ለማላቀቅ የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

ተመራቂዎች ጠባቂ ሳይሆኑ አጋጣሚውን ሁሉ በመጠቀም ስራ ፈጥረው ወደ ተግባር መግባት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ከወሎ ህዝብ ያገኙትን የአንድነትና አብሮናት ተምሳሌትም በሌሎች አካባቢዎች በማስፋት ይህኑን የማስጠበቅ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው በክልሉ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች አስፈላጊውን ሁሉ ጥበቃ በማድረግ ተማሪዎች ያለ ስጋት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መንግስት ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ህዝብ አቃፊ እንጂ የሴራ ፖለቲከኞች እንደሚያወሩት ጨቋኝ አለመሆኑን በተግባር ያያችሁ ተማሪዎች እውነታውን በምትሄዱበት አካባቢ ሁሉ ማስረዳት ይኖርባችኋል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታምሬ ዘውዴ እንደገለጹት ዛሬ ካስመረቋቸው ተማሪዎች መካከል 42  በመቶ ሴቶች ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ወቅታዊ ችግሮችን ተቋቁሞ ተማሪዎች ተገቢውን እውቀት ጨብጠው የጀመሩትን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ በማድረግ ለዚህ ዕለት ማብቃታቱንም አስረድተዋል።

ተመራቂዎች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለምረቃ የበቁ በመሆናቸው ባገኙት እውቀት ህዝባቸውንና ሃገራቸውን በቅንነትና ታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ምንም እንኳ አስቸጋሪ ወቅት ቢሆንም ተቋቁመን ከዚህ በመድረሳችን ተደስተናል ያለችው ደግሞ ተመራቂ አበበች ያለው ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም