ቀጥታ፡

በዳያስፖራ ተሳትፎ ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የበጎ ተግባራት ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2013 ( ኢዜአ) በተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ በዳያስፖራው ተሳትፎ ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የበጎ ተግባራት መከናወናቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ገለጸ።

ኤጀንሲው በበጎ አድራጎት ፕሮጀክቶች ቀረጻ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለሁለት ቀናት የሚቆይ አውደጥናት በቢሾፍቱ እያካሄደ ነው፡፡

ዳያስፖራው በግለሰብና በተናጠል የሚሰጠውን የማኅበረሰብ አገልግሎት በማቀናጀት መምራት እንደሚገባ ኤጀንሲው በዚሁ ጊዜ አስገንዝቧል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ እንዳሉት ኤጀንሲው ዳያስፖራው በበጎ አድራጎት የማኅበራዊ አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት የሚያደርገውን እገዛ በማስተባበር አመርቂ ተግባር እያከናወነ ነው፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በአገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች እንዲሁም ፕሮጀክቶች ላይ ሚናውን ሲወጣ ቆይቷል ብለዋል፡፡

ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም ከ560 በላይ የዳያስፖራ አባላት የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ዳያስፖራው በ2013 በጀት ዓመት ስድስት ወራትም ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ በጎ ተግባራት ማከናወኑንም ተናግረዋል።

በጎ ተግባራቱ ነጻ የሕክምና አገልግሎት፣ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም የመሰረተ ልማት አቅርቦትን ያካተቱ ናቸው።

በአውደ ጥናቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ ሊሰራ እንደሚገባ በትምህርት ሚኒስቴር በቀረበ ሰነድ ተመላክቷል፡፡

በዛሬው መድረክ ዳያስፖራው ትምህርት ቤቶቹ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አቀናጅቶ ለመምራት በሚቻልበት ሁኔታም ውይይት ተካሂዷል፡፡

በአገሪቷ ገጠራማ አካባቢዎች የትምህርት ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች ቀረጻ ላይም እንዲሁ፡፡

በአውደ ጥናቱ የፌዴራል ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች፣ የዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶች፣ የክልል ትምህርት ቢሮዎችና የትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች እየተሳተፉ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም