ለቤተክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ጥረት ማድረግ ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ለቤተክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ጥረት ማድረግ ይገባል ተባለ
አሜሪካ ሀምሌ 16/2010 ለቤተክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋን ለማምጣት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የእርቅ ልኡካን ቡድን በአሜሪካ ከሚገኘው ሲኖዶስ ጋር የእርቅና የሰላም ጉባኤ ካህናት፣ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የመጡ ምዕመናን በተገኙበት ተካሂዷል። በቀጣይ ቀናትም ሊቀ-ጳጳሳት፣ካህናትና ሽማግሌዎች ስለ ቤተክርስቲያን እንድነት በመፀለይና ውይይት በማድረግ እንደሚቆዩ ታውቋል። ጉባኤው በፀሎት ስነ-ስርዓት የተጀመረ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቤተክርስቲያኒቷ አንድነት እንዲመጣ የሰጡት ትኩረት አድናቆትና ውዳሴ የሚሰጠው መሆኑን ተሳታፊዎች ጠቁመዋል። በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን እንደገለጹት በሰላምና እርቁ ውይይት ወቅት ከራስና ከሌላ ወገን የሚመጣ ይቅርታን በመቀበል አንድ ሆኖ ወደፊት ለመራመድ የሚያስፈልገውን ሁሉ በመያዝ ኢትዮጵያ ከፍ ብላ እንድትታይ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል። በተለይም ይህንን የእርቅ ጉዳይ ለማስፈጸም ኃላፊነት የተቀበሉ አባቶችና የእርቅ ኮሚቴ አባላት ሁሉ የኋላቸውን ሳይሆን የወደፊቱን በማየት ለቤተክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋን ለማምጣት ጥረት ማድረግ ይገባል ብለዋል። በተያያዘ ዜናም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ እየታየ ላለው ለውጥና በተለይም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት የኢትዮጵያና የኤርትራ የወንጌል አማኞች በአሜሪካ ምስጋና አቅርበዋል። አማኞቹ ከዋሽንግተን ዲሲ፣ከሜሪላንድና ከቨርጂኒያ በዋሽንግተን ዲሲ የአለም አቀፍ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በመሰባሰብ ነው የምስጋና ስነ-ስርዓቱን ያከናወኑት። የቤተክርስቲያኒቷ ሲኒየር ፓስተር አንፋሬ አሊጋዝ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይዘውት የመጡት የፍቅር፣ የሰላም ፣የይቅርታ መልእክት መቼም የማይወድቅና አሸናፊ ነው። በአገራቱ መካከል የነበረው አለመግባባት እንዲፈታ ቤተክርስቲያኒቱ ላለፉት 20 ዓመታት ያለማቋረጥ ስትጸልይ እንደነበር አስታውሰዋል። የፀሎትና የምስጋና ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው ለዓመታት ተራርቆ የቆየ ወንድማማችነትን መልሶ አንድ ሲሆን መመለክት እንደሚያስደስት ተናግረው የሰላም ዋጋው ከምንም አንደሚበልጥ አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች በተወጠረችበት ጊዜ የወንጌል አማኖች ልመናቸውን በጸሎትና በምልጃ አስተዋጾአቸውን እንዳላቋረጡ ሁሉ አሁንም በጸሎትና በተግባር የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካ የሚያደርጉት ውይይት የተሳካ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።