የህወሃት መወገድ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላምና አንድነት ወሳኝ መሆኑን በአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

42

አሶሳ፣ ጥር 07 / 2013(ኢዜአ) የህወሃት ጁንታ መወገድ ኢትዮጵያን ወደ ዘላቂ አንድነት እና ሠላም ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን በአሶሳ ከተማ አስያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አብረሃም ኪቲላ እንዳሉት ህወሃት ሃገርን የማፈራረስ ራዕይ አስቀምጦ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው አስነዋሪ ጥቃት የዚሁ ዋነኛ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ድርጊቱ አሳዛኝ ቢሆንም ቡድኑ ከህግ ተጠያቂነት ማምለጥ እንዳልቻለ ጠቁመው የህግ የበላይትን ለማስፈን የጥፋት ቡድኑ ቁንጮዎች ታድነው መያዝ እና እምቢተኞች ደግሞ መደምሰሳቸው እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

ህወሃት ረጃጅም የጥፋት እጆች እንደነበሩት ያስታወሱት አቶ አብረሃም በመተከል እና ሌሎች አካባቢዎች የቀጠለው ጥቃት የቡድኑ የጥፋት እቅድ ቅሪት ነው ብለዋል፡፡

የጁንታው  መወገድ ለሃገር ዘላቂ ሠላም እንደሚበጅ  ገልጸው መንግስት  ህገመንግስቱ የሁሉንም ኢትጵያዊ ጥቅም በሚያስጠብቅም መልኩ እስከ ማሻሻል መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ታፈሰ ፉፋ በበኩላቸው  በድኑ ለ27 ዓመታት ከህግ በላይ የሆነ እስኪመስል ጥፋት ሲፈጽም መቆየታቸውን አውስተዋል፡፡

በጁንታው ላይ የተወሰደው እርምጃ በሃገሪቱ የህግ የበላይነት በተግባር አሳይቷል ብለዋል፡፡

የዜጎችን አብሮ የመኖር የቆየ ባህልን በማጎልበት ዴሞክራሲ እንዲዳብር ወሳኝ እንደሆነም አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው በሠላም ወጥተው እንዲገቡ ዋስትና ይሰጣል ሲሉም አቶ ታፈሰ አስረድተዋል፡፡

ህብረተሰቡ፣ መንግስት እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጥቃቅን ልዩነቶቻችን ይልቅ  አንድ በሚያደርጉን ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለባቸው ብለዋል፡፡

አሁንም በሃገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች የሚፈጸሙ ግድያዎች መቆም አለባቸው ያሉት ደግሞ  ወይዘሮ ዘይነብ ሳሂር ናቸው፡፡

ለዜጎች ከምንም በላይ ተቀዳሚና  አስፈላጊው ጉዳይ ሠላም እንደሆነ የገለጹት አስተያየት ሰጪዋ በጁንታው ላይ እየተወሰደ የሚገኘውን እርምጃ ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ድጋፉን ማጠናከር ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

አስር አለቃ አበባው ወንድምአገኘው ህወሃት በህዝብ ላይ ሲፈጽም በነበረው ግፍ ምክንያት ፈጣሪ መጨረሻውን እንዲሳያቸው ሲጸልዩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የጁንታው ህወሃት መወገድ ምክንያት የህዝብ እና የመንግስት ቅንጅት ብቻ ሳይሆን የፈጣሪ ከፍተኛ ድጋፍም አለበት ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተለያየ ጊዜያት  የተከሰተው ግጭት ላስከተለው ሞት፣ መፈናቀል እና ንብረት ውድመት ምክንያቱ ይኸው የጥፋት ቡድን  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የህወሃት መወገድ በቀጣይ በኢትዮጵያ የምንመኘውን ሠላም ፣ አንድነት እና ፍቅር ያመጣል ብዬ አምናለሁ ሲሉ አስር አለቃ አበባው ገልጸዋል፡፡

በሃገሪቱ ሌላ ጁንታ እንዳይፈጠር መጠንቀቅ አለብን ፤ በተለይ መንግስት ሹማምንቱ በህዝብ አንድነት የሚያምኑ መሆናቸውን ሊያረጋግጥ ይገባል ብለዋል፡፡

አመራሮችም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን የሃገር ፍቅር መሠረት ያደረገ የአመራር ጥበብ አርአያ አድርገው መስራት እንዳለባቸውም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም