የወረዳው ካቢኔ የወሰነልኝን የመኖሪያ ቤት ቅያሬ ክፍለ ከተማው ነጥቆ ለሌላ ግለሰብ ሰጠብኝ- ቅሬታ አቅራቢ

86

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2013 ( ኢዜአ)  በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 ካቢኔ የወሰነላቸውን የመኖሪያ ቤት ቅያሬ ክፍለ ከተማው ለሌላ ግለሰብ እንዳስተላለፈባቸው አንድ ቅሬታ አቅራቢ ግለሰብ ገለጹ።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት በበኩሉ የቅሬታ አቅራቢዋ ጥያቄ ትከክል ነው በቅርቡ መፍትሔ ለመስጠት አማራጮች አሉኝ ብሏል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት በበኩሉ የቤት ቅያሬ ጥያቄውን በጥልቀት ሳይረዳ በመመሪያው መሠረት ለሌላ ግለሰብ ቢያስተላልፍም የቅሬታ አቅራቢዋን ችግር ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በቅርቡ መፍትሔ ለመስጠት አማራጮች አሉን ብሏል።

ለኢዜአ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ወይዘሮ አስቴር ማሞ በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ስሙ ዘበኛ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ናቸው።

በ2010 ዓ.ም የልማት ተነሺ ሆነው ከወረዳ 5 ወደ ወረዳ 4 በተሰጣቸው ተለዋጭ ቤት አንድ አካል ጉዳተኛ ልጃቸውን ጨምሮ ስድስት የቤተሰብ አባላትን ይዘው ይኖራሉ።

ወደዚህ መኖሪያ ቤት ሲዛወሩ በተለይ ለአካል ጉዳተኛ ልጃቸው የማይመች በመሆኑ በእለቱ ቅሬታቸውን ቢያሰሙም "ለጊዜው ይኑሩበት ተለዋጭ ቤት እናዘጋጅለዎታለን" የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸው እስካሁንም በችግር እየኖሩ በመሆኑን ይናገራሉ።

ጊዜ ወስዶም ቢሆን አሁን ላይ ችግራቸው እንዲፈታ የወረዳ 4 ካቢኔ የመኖሪያ ቤት ቅያሬ ቢፈቅድላቸውም የአራዳ ክፍለ ከተማ ነጥቆ "ለመንግስት ሹመኛ" ስለሰጠባቸው መፍትሄ እሻለሁ ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

በቤቱ ጥበትና በተለይ ደግሞ ለአካል ጉዳተኛ ልጃቸው በማይመች ሁኔታ ሆኖ ከቤት ወደ ትምህርት ቤት ለማመላለስ ተቸግሬያለሁ እልባት ይሰጠኝ ሲሉ ጠይቀዋል።

ወይዘሮ አስቴር የወረዳው ካቢኔ ቤቱ ይሰጣት በሚል ወስኖ በስማቸው የተመዘገበውን ቤት ክፍለ ከተማው ለሌላ ግለሰብ በመስጠቱ ማዘናቸውንም ገልጸዋል።

የወረዳ 4 ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ዋለ፤ ግለሰቧ አሁን የሚገኙበት ቤት በተለይ ለአካል ጉዳተኛ ልጃቸው የማይመች መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዚህም ምክንያት ተመጣጣኝ ቤት እንዲቀየርላቸው ለወረዳው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ካቢኔው የቤት ቅያሬው እንዲፈቀድላቸው መወሰኑን ገልጸዋል።

የወረዳው ካቢኔ ህዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም በወረዳው በቤት ቁጥሩ 254 በተመዘገበ ቤት እንዲኖሩ በሙሉ ድምጽ አፅድቆ የውሳኔ ሐሳቡን ለክፍለ ከተማው መላኩን አስታውቋል።

የካቢኔውን የውሳኔ ሐሳብ ብንልክም በመንግሥት ቤቶች አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 5/2011 መሠረት የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጠው በክፍለ ከተማው በመሆኑ መኖሪያ ቤቱ ለወይዘሮ አስቴር ሳይሰጥ ለአንድ አመራር ተላልፏል ብለዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዲ ሙሉነህ በበኩላቸው የቅሬታ አቅራቢዋ ጥያቄ ትክክል መሆኑን ገልጸው መፈትሄ ይሰጣቸዋል ብለዋል።

ግለሰቧ ያቀረቡት ቅሬታ ትክክል ነው "ጉዳዩን በጥልቀት ሳንረዳ ቤቱ ለሌላ ግለሰብ ተላልፏል" ሲሉ አረጋግጠዋል።

ጽህፈት ቤቱ መመሪያውን ተከትሎ ቤቱን ለአንድ አመራር ማስተላለፉን አስታውሰው የግለሰቧ ችግር አሳሳቢ መሆኑ ስለታመነበት ቀጣይ የመፍትሔ አማራጮች እንደሚያስቀምጡ ገልጸዋል።

ክፍለ ከተማው የግለሰቧን ችግር ተመልክቶ አካል ጉዳተኞችን ለማገዝ አመቺና ተመጣጣኝ ቤት በቅርቡ ይቀየርላቸዋል ሲሉም አቶ አብዲ አረጋግጠዋል።

የቤት ቅያሬው የቀበሌ ቤቶችን ለማስተዳደር በወጣው መመሪያ ቁጥር 5/2011 መሠረት ለልማት ተነሺ፣ በፍርድ ቤት ለተወሰነላቸው እና ለአመራር ቅድሚያ እንደሚሰጥ መመሪያው ያስቀምጣል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም