ኤጀንሲው ደረቅ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል 52 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

70

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2013 ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ በስድስት ወራት ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል 52 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለፀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር እሸቱ ለማ እንደተናገሩት "አካባቢን ከማፅዳት ባለፈ ቆሻሻን ሰብስቦ መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል የገቢ ምንጭ ማድረግ ተችሏል፡፡

ከዚህ ባለፈ ወጣቶችን በማደራጀትና ወደ ስራ በማስገባት ደረቅ ቆሻሻን ወደ ማዳበሪያነት በመቀየርና ፕላስቲክን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል የማድረግ  ስራ መሰራቱን አብራርተዋል፡፡

በዚህም በበጀት አመቱ ስድስት ወራት 52 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ዶክተር እሸቱ ገልጸዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ከ1 ሺህ በላይ ወጣቶችን በዚሁ ስራ ላይ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆናቸውንም እንዲሁ፡፡

ቆሻሻን በተገቢው መንገድ ሰብስቦ ማስቀመጥ ከተቻለ ሀብት መሆኑን የተናገሩት ዶክተር እሸቱ ይህ ካልሆነ ግን የጤና ጠንቅ በመሆን ኑሮን ያዛባል ብለዋል፡፡

በባለፈው አመት ደረቅ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም 89 ሚሊዮን ብር መገኘቱንም አስታውሰዋል፡፡

ከተማን ውብና ፅዱ ማድረግ በአንድ ተቋም ብቻ ተሰርቶ የሚሳካ አለመሆኑን ገልጸው በተለይ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ሰዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

ከተማዋ ውብ ሆና በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን ህብረተሰቡ የአካባቢን ማፅዳት ስራውን የእለት ከእለት ተግባሩ ማድረግ አለበትም ነው ያሉት።

በኤጀንሲው የግንዛቤ ስርፀትና የህዝብ ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ነሜ እንደሚሉት ከከተማዋ በቀን በአማካይ ከ2 ሺህ 500 ቶን ያላነሰ ቆሻሻ ይሰበሰባል።

በመሆኑም የሚወገድ ቆሻሻን ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት መጠቀም ከተቻለ 80 በመቶ የሚሆነውን ቆሻሻ ሀብት ማድረግ ይቻላል ብለዋል።  

በከተማዋ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብረሃም ታደሰ በበኩላቸው አካባቢን ማፅዳት አንዱ የበጎ አድራጎት ተግባር በመሆኑ ወጣቶች በተደራጀ መንገድ ዘላቂ የሆነ የፅዳት ስራ እንዲያከናውኑ ይደረጋል ብለዋል።

በቅርቡ በመዲናዋ 28 ሺህ 162 ዜጎች በተቀናጀ የከተማ ውበት፣ አረንጓዴ ልማት፣ በከተማ ግብርና፣ በደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብና በሌሎች የስራ ዘርፎች ሰልጥነው ለስራ ዝግጁ መሆናቸው ይታወቃል ።

በዚህም የስራ እድል ከተፈጠረላቸው  28 ሺህ 162 ዜጎች 53 ነጥብ 3 በመቶ ሴቶች መሆናቸውና 5 ሚሊዮን ካሬ መሬት የመስሪያ ቦታና  ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ስራ ማስኬጃ  በጀት ከአስተዳደሩ ተመድቦላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም