ምርጫው ሰላማዊና ፍትሀዊ እንዲሆን የምክር ቤት አባላት ኅላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

37

ሀዋሳ፣ ጥር 7/2013 (ኢዜአ)- ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሀዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በየደረጃው የሚገኙ የምክር ቤት አባላት አርአያነት ያለው ተግባር መፈጸም እንዳለባቸው የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሳሰቡ።

አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ሄለን ደበበ የክልሉ ምክር ቤት 5ኛ ዙር 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ አስቸኳይ ጉባኤን ሲከፍቱ እንዳሉት ምርጫው በመላው ህዝብ ተሳትፎ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ምክር ቤቶች ትልቅ ሀላፊነት አለባቸው።


መንግስት ህገ ወጡ የህወሀት ጁንታ የፈጸመውን የሀገር ክህደት ወንጀል በመመከት ህግ የማስከበር ዘመቻውን በድል ባጠናቀቀበት ማግስት ጉባኤው መካሄዱ ልዪ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

"የህገ ወጡን የህወሀት አላማ ለማክሸፍ ከፍተኛ መሰዋዕትነት የከፈለው የመከላከያ ሰራዊት ክብር ይገባዋል" ብለዋል።


በከፍተኛ መሰዋዕትነት የተገኘውን ድል በመጠበቅ መጪውን ምርጫ በስኬት ለማጠናቀቅ የምክር ቤቱ አባላት አርአያ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።


ለአንድ ቀን በሚካሄደው ጉባኤ በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤት አባላትን ቁጥር ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ እንዲሁም የተጨማሪ በጀት መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።


በጉባኤው የስራ አስፈፃሚ አባላትና የዳኞች ሹመትም እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም