በመዲናዋ ወንጀል እየተፈፀመ ስለሆነ የውጪ ሀገራት ዜጎች ወደ ተጠቀሰው ስፍራ ጉዞ እንዳያደርጉ በሚል የተናፈሰው ዜና የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ መሆኑን ፖሊስ ገለጸ

67

አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2013(ኢዜአ) ወንጀል በስፋት እየተፈፀመ ስለሆነ የውጪ ሀገራት ዜጎች ወደ ተጠቀሱት ስፍራዎች ጉዞ እንዳያደርጉ በማለት በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን እና ማህበራዊ ሚዲያዎች የተናፈሰው ዜና የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ እንደሆነና የከተማዋ የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ መሆኑንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡

ታህሳስ 18 ቀን 2013 ዓ.ም አንድ የውጪ ሀገር ዜጋ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ጉለሌ የዕፅዋት ማዕከልን በመጎብኘት ላይ እንዳሉ ስድስት ግለሰቦች በስለትና በዱላ በማስፈራራት ሁለት ቀለበት፣ 2 ሞባይልና 4ሺ ብር ቢወሰዱባቸውም ፖሊስ ባደረገው ክትትል ወንጀሉን ፈፅመዋል ያላቸውን ተጠርጣሪዎች መያዙንም ተገልጿል።

ኮሚሽኑ እንደጠቀሰው ወንጀል የተፈፀመባቸው የውጪ ሀገር ዜጋ ተጠርጣሪዎቹን በአካል ቀርበው በመለየት እንዲያረጋግጡ ቢጠየቁም በልዩ ልዩ ምክንያት ያልቀረቡና ፖሊስ ከአካባቢው ሌሎች ተጨማሪ ማስረጃዎችን እያሰባሰበ ነው፡፡

ስፍራው በጣም ሰፊ እና ሰዋራ በመሆኑ መሰል የወንጀል ድርጊቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችል የተፈፀመው የወንጀል ድርጊትም እየተጣራ መሆኑን አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ስለ አካባቢው የፀጥታ ሁኔታ ከኮሚሽኑ በቂ መረጃ ሳይጠይቁ በስማ በለው ያገኙትን መረጃ በተዛባ መልኩ እያቀረቡ መሆኑንም ተጠቅሷል።

በስማ በለው ያገኙትን መረጃ መነሻ በመድረግም የከተማዋ ፀጥታ አስተማማኝ እንዳልሆነ በተለይ ደግሞ በእንጦጦ ፓርክ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ መንቀሳቀስ ስጋት እንደሆነ አድርገው መዘገባቸው ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ሊታረም ይገባል ብሏል፡፡

በቅርቡ የተከበረው የገና በዓል በሰላም መከበሩንና ከ12ሺ በላይ ሰዎች የታደሙበት ታላቁ ሩጫ ያለምንም የፀጥታ ችግር መጠናቀቁ የከተማዋን ሰላማዊነት ማሳያ ስለመሆኑ ኮሚሽኑ አስታውሶ፤ በተጠቀሱት ስፍራዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ በመሆኑ ሰዎች በጋራም ሆነ በግል ጉብኝት እያደረጉ እንደሚገኙ ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም