ተመድ ኢትዮጵያ የውስጥ አንድነቷን ለማጠናከር የጀመረችውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ተመድ ኢትዮጵያ የውስጥ አንድነቷን ለማጠናከር የጀመረችውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታወቀ
አዲስ አበባ ሃምሌ 16/2010 የኢትዮጵያ መንግስት አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የጀመረውን የለውጥ ሂደት የሚደግፍ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ። በኢትዮጵያ የተመድ ተጠሪ አሁና ኢዚያኮንዋ ኦኖች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የውስጥ አንድነቷን ለማስጠበቅ የምታደርገውን የለውጥ ሂደት ድርጅቱ ይደግፋል። ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦችና ኃይማኖቶች ብዝሃነትን እንዲሁም የተለያዩ ፍላጎቶችን በማስተናገድ ረገድ ለሌሎች አገሮች አርአያ መሆኗን አመልክተዋል። ለአገሪቱ የሚበጀው ለጋራ ዓላማ የሚቆም አንድነትን ማጎልበት መሆኑን የተናገሩት የተመድ ተጠሪ መነጣጠል ለችግር እንደሚዳርግ አስገንዝበዋል። በኢትዮጵያ የተካሄደውን የስልጣን ሽግግር ተከትሎ ወደኃላፊነት የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአገሪቱን አንድነት ለማጠናከር የጀመሩት እንቅስቃሴ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል። “በህዝቦች መካከል አንድነት በሌለበት ሁኔታ ዘላቂ ዕድገት ማምጣት ከባድ ነው” ያሉት ተጠሪዋ ኢትዮጵያ ውስጥ በአዲሱ አመራር የተጀመረው የለውጥ ሂደትና ችግሮችን የማስታረቅ ጥረት የአገሪቱን ዕድገት ለማስቀጠል የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል። በአገሪቱ እየተካሄደ ባለው የለውጥ ሂደት የተመድ ደስተኛ መሆኑን ጠቅሰው መንግስት በአገሪቱ እርቅና ሰላም ለማውረድ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የተመድን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት አስፈላጊ መሆናቸውን ገልፀዋል። በመሆኑም የለውጥ ሂደቱ ይቀጥል ዘንድ ተመድ አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኢዚያኮንዋ ኦኖች አረጋግጠዋል። በአሁኑ ወቅት አዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት አመራር የውስጥ አንድነት ከማጠናከር ባሻገር በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ትብብር ለማምጣት እያደረገ ያለውን ጥረት ተጠሪዋ አድንቀዋል። በአፍሪካ ቀንድ የነበረው ግጭት በቀጠናው ምቹ የሆነ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዳይኖር ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤት አገሮች ያለውን ትብብር ለማጠናከርና ቀጣናውን ወደ አንድ ለማምጣት የጀመሩት ጥረት ለአካባቢው ሰላምና ልማት መልካም ዕድል መሆኑንም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የተመድ ተጠሪዋ አክለውም አገሪቱ የገጠማት የውስጥ ፈተና ሳይበግራት ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ሚናዋን እየተወጣች መቀጠልዋንም አድንቀዋል። አገሪቱ በአካባቢውና በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደረገች ያለችው አስተዋፅኦ ለሌሎች የዓለማችን አገሮች ምሳሌ ሊሆን የሚችል መሆኑን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ በነበራቸው የሶስት ዓመታት ቆይታ አስደሳች ጊዜ እንደነበራቸው የገለጹት ተጠሪዋ አሁና ኢዚያኮንዋ ኦኖች ለተመድ የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ዳይሬክተርነት ታጭተዋል። በአዲሱ የኃላፊነት ጊዜያቸውም ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።