የደቡብ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተመሠረተ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተመሠረተ

ሀዋሳ ጥር 06/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀዋሳ ከተማ በካሄዱት ስብሰባ የጋራ ምክር ቤት በመመሥረት የቃል ኪዳን ሠነድ ተፈራርሙ።
ምክር ቤቱን የመሠረቱት የደቡብ ክልል ብልጽጋና ፓርቲን ጨምሮ በሀገርና ክልል ደረጃ የሚፎካከሩ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ናቸው።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በምርጫ ሂደት ውስጥ በሚኖሯቸው ግንኙነቶች ውስጥ ሊገዙባቸው በሚችሉ መመሪያዎችና ደንቦች እንዲሁም በሚያከናውኗቸው የጋራ ሥራዎች ዙሪያ ትናንት ከተወያዩ በኋላ የጋራ ምክር ቤቱን መስርተዋል።
ፓርቲዎቹ የጋራ ቃል ኪዳን ሠነድም ተፈራርመዋል።
ከተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች መካከል አቶ ተክሌ ቦረና ምክር ቤቱ በመመሥረት የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ መፈረማቸው መጪውን ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሠላማዊና ፍትሐዊ ለማድረግ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
የምርጫ ሥራዎች በዋናነት የሚከናወኑት በክልል ደረጃ ሳይሆን በወረዳ ባሉ የምርጫ ክልሎች ነው ያሉት አቶ ተክሌ በሂደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅርበትና ፍጥነት ለመፍታት ምክር ቤቱ በታችኛው መዋቅሮችም ቢመሠረት የተሻለ እንደሚሆን አስረድተዋል።
ሌላው የፓርቲ ተወካይ አቶ አለሳ መንገሻ በበኩላቸው ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሂደቱን ጠብቆ እንደሚካሄድ የሚጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ችግሮች ቢያጋጥሙ ለመፍታት በጋራ መስራታቸውና በፈረሙት የቃል ኪዳን ሰነድ መገዛታቸው ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።
መንግስት በዚህ ምርጫ ሂደት ውስጥ የሚገጥሙ ችግሮች ለማለፍና ሀገራዊ ለውጡን ለማሳካት በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመው የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለሕግና ሕገ-መንግስቱ ተገዢ ልንሆን ይገባል ብለዋል።
ምክር ቤቱን ከማቋቋም ባለፈ በሙሉ አቅሙ ተንቀሳቅሶ ለችግሮቹ መፍትሔ እየሰጠ እንዲሄድ ብሎም ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ ሌላው የፓርቲ ተወካይ አቶ መርዕድ ሽብሩ ናቸው።
ለዚህም በተለይ ከመንግስት በኩል ለምክር ቤቱ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የብልጽግና ተወካይ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል እውነተኛ ዴሞክራሲን ማምጣት ለሌሎች የለውጥ ሂደቶች መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በማመን ነው እየሰራን ያለነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት በተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩል ሲነሳ የነበረውን የመንግስትና ፓርቲ ሚና መደበላለቅ ችግር ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የምክክር መድረኩን የመሩት የደቡብ ክልል ብልፅግና ፓርቲ የሲቪክ ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር አንተነህ መሉ በበኩላቸው የጋራ ምክር ቤቱ የተመሰረተው በፌዴራል ደረጃ ያለውን የለውጥ ሂደት በክልል ደረጃ ለማስቀጠል በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እንደሆነ ገልጸዋል።
በቀጣይም በታችኞቹ መዋቅሮች ላይም የጋራ ምክር ቤት ዕውን እንዲሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ መንግስት በኩል ለምክር ቤቱ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ለማድረግ በሚቻልበት ዙሪያም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የምክር ቤቱ አመራር አካላት በቅርብ በሚደረግ ስብሰባ እንደሚመረጡ በመድረኩ ተገልጿል።