በተሽከርካሪ ተደብቆ ሲጓጓዝ የነበረ 2 ሺህ 525 ተተኳሽ ጥይት ተያዘ

81

ደሴ ጥር 6/2013 (ኢዜአ)- በህገ ወጥ መንገድ በተሽከርካሪ ተደብቆ ሲጓጓዝ የነበረ 2 ሺህ 525 ተተኳሽ የክላሽ ጥይት መያዙን የፌደራል ጉምሩክ ኮሚሽን ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ አስታወቀ።

የቅርንጫፉ የደንበኞች ትምህርትና ስልጠና ቡድን መሪ አቶ አሳምነው አዳነ ለኢዜአ እንደገለጹት ተተኳሽ ጥይቱ የተያዘው ትላንት ለሊት በወልዲያ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በተደረገ ፍተሻ ነው።

ጥይቱ ከአላማጣ ወደ ባህር ዳር በመጓዝ ላይ በነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ  ኮድ 3 -06546 አማ  በሆነ አይሱዚ የጭነት ተሽከረካሪ በሽንኩርት ውስጥ ተደብቆ ሊያልፍ ሲል በፍተሻ መገኘቱን ተናግረዋል።

ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በተደረገ ትብብር አሽከርካሪውን ጨምሮ ሦስት ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን አመልክተዋል።

ቅርንጫፉ በህገወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ የጦር መሳሪያዎችን የመያዝ ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉን ቡድን መሪው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም