ኢንስቲትዩቱ ከሳተላይት የሚገኙ መረጃዎችን በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እንዳለበት ተጠቆመ

62

አዲስ አ በባ፤ ጥር 6/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ስፔስ ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከሳተላይት የሚገኙ መረጃዎችን በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጠቁሟል።

ቋሚ ኮሚቴው የኢንስቲትዩቱን የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ በዛሬው ዕለትየመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እምዬ ቢተው በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ባለመስራቱ ከሳተላይት የሚገኙ ለሀገር ፋይዳ ያላቸው መረጃዎች አጥጋቢ የግንዛቤ ሥራ ባለመሰራቱ ወደ ተጨባጭ ተግባር አየተቀየሩ አይደሉም።

የስፔስ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሀገር ያለውን ፋይዳ በተመለከተ ለማሕበረሰቡ ከማስተዋወቅ አንጻርም ኢንስቲትዩቱ ክፍተት አንዳለበትም ሰብሳቢዋ አንስተዋል።

የኢንስቲትዩቱን ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ዓቅም ለመገንባት አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ባለሙያዎቹ ፣ አግባብነት ያለው የትርፍ ሰዓት ክፍያ እየተከፈላቸው እንዳልሆነ ማንሳታቸውን የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ ኢንስቲትዩቱ በአሠራር ፣ በመመሪያና አደረጃጀት መፈታት ያለባቸውን ጉዳዮች ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን መፍታት አለበት ብለዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ከባለሙያዎቹ ጋር በነበረው ውይይት ኢንስቲትዩቱ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት እያንቀሳቀሰ እያለ ለኮሮና ቫይረስ የሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው ፣ አስፈላጊው የመከላከያ ግብዓት ለባለሙያዎቹ መቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ በበኩላቸው ፣ ኢትዮጵያ በአውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2020 በአፍሪካ ብቸኛዋ ሳተላይት ያመጠቀች ሀገር መሆኗን ገልጸው ፣ በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ አስተያየቶችና ክፍተቶችን ለቀጣይ ለመፍታት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማህበራዊ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም