ኢትዮጵያ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 64 አትሌቶችን ታሳትፋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 64 አትሌቶችን ታሳትፋለች
አዲስ አበባ ሀምሌ16/2010 ከሐምሌ 25 እስከ 29 ቀን 2010 ዓ.ም በናይጄሪያ አሰባ ከተማ በሚካሄደው 21ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 64 አትሌቶችን እንደምታሳትፍ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። በሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያ በ34 ወንዶችና በ30 ሴት አትሌቶች እንደምታሳትፍ የተገለጸ ሲሆን በ19 የውድድር አይነቶች በሁለቱም ጾታ ትወዳደራለች። በናይጄሪያ በሚካሄደው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፈው ቡድን ለአንድ ወር ያክል በሆቴል ተቀምጦ የአየር ንብረቱ ከውድድር ስፍራው ጋር ተቀራራቢ በሆኑ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ጠንካራ ልምምድ እያደረገ መሆኑን ፌዴሬሽኑ ገልጿል። የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን ደቡብ አፍሪካ ደርባን ላይ በተካሄደው 20ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ1 ወርቅ፣ 2 ብር፣ 3 ነሐስ በጠቅላላ በ6 ሜዳልያ ከተሳተፉ የአፍሪካ ሃገራት 8ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች። በዚያን ወቅት ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለሃገሩ ያስገኘው አትሌት ጫላ በዩ ሲሆን የተወዳደረበት ርቀት ደግሞ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ነበር። ኢትዮጵያ በ3ኛውና በ10ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ባትሰለፍም በሌሎቹ ሻምፒዮናዎች ላይ ተሳትፋለች። እስካሁን በተሳተፈችባቸው ሻምፒዮናዎች 40 የወርቅ፣ 47 የብርና 54 የነሐስ በድምሩ 141 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች። እ.አ.አ. በ1979 ዓ.ም በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማርሽ ቀያሪው አትሌት ምሩጽ ይፍጠር በ5 እና 10 ሺህ ወርቅ እንዲሁም ሰሞኑን ህይወቱ ያለፈው አትሌት ከበደ ባልቻ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት በአጠቃላይ 3 ወርቅ ለአገራቸው ማስገኘት ችለዋል።