አድዋና አክሱም ከተሞች በቅርቡ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
አድዋና አክሱም ከተሞች በቅርቡ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2013(ኢዜአ) በትግራይ ክልል አድዋና አክሱም ከተሞች በቅርቡ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በምዕራብ ትግራይ የኃይል አቅርቦቱን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተቋሙ ገልጿል።
የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሞገስ መኮንን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ በክልሉ የሕግ ማስከበሩ ሥራ ከተጀመረ በኋላ ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመሮች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተናግረዋል።
በዚህም በአላማጣ በኩል አድርጎ በአሸጎዳ ወደ መቀሌ የሚገባው እንዲሁም ከተከዜ ተነስቶ በመቀሌ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚሄደው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
በአንዳንድ ቦታዎች ጉዳቱን በፍጥነት ጠግኖ ወደ አገልግሎት ለመመለስ አስቸጋሪ እንደሆነም ገልፀዋል።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ፈታኝ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ሞገስ የባለሙያዎች ቡድን የጥገና ስራውን በሁለት ተከፍሎ እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህም አንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ቶሎ ሲያገኙ በአንዳንድ ቦታዎች የደረሰው ጉዳት መጠኑ ከፍ ያለ በመሆኑ የጥገና ሥራው ጊዜ መውሰዱን አብራርተዋል።
እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ ተቋሙ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ጉዳት የደረሰባቸው መስመሮች ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ እየተሰራ ነው።
በምስራቅ ትግራይ ያሉ ከተሞች አብዛኞቹ ኤሌክትሪክ ማግኘት መጀመራቸውን ያስታወሱት ኃላፊው በተለይም አላማጣ፣ መሆኒና መቀሌ አካባቢዎች ኃይል ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በምዕራብ ትግራይ በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮቹ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ አካባቢው የእንቅስቃሴ ገደብ ያለበት በመሆኑ የጥገና ስራውን ፈጥኖ ማከናወን አለመቻሉን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በአድዋና አክሱም አካባቢዎች በቅርቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
አክሱም፣ አድዋ፣ ሽሬ እና ሽራሮ ከተሞች የጥገና ሥራው በስፋት ከሚካሄድባቸው መካከል መሆናቸውን ጠቅሰው "የተለየ ችግር እስካላጋጠመ ድረስ አድዋና አክሱም በቅርቡ ኃይል ያገኛሉ ብለን እናስባለን" ብለዋል።
አቶ ሞገስ የክልሉ ነዋሪዎች የጥገና ሥራውን ለሚያከናውኑ ባለሙያዎች ተገቢውን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።