ቀጥታ፡

የጁንታው ቁልፍ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ለዘላቂ ሰላምና የህግ የበላይነት መከበር ፋይዳው የጎላ ነው ... የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2013(ኢዜአ) የህወሃት ጁንታ ቁልፍ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና የህግ የበላይነት መከበር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለፁ።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና ሌሎች የፌደራል ጸጥታ ተቋማት በጋራ እያከናወኑት ባለው ወንጀለኞችን የማደን ዘመቻ በቁጥጥር ስር የዋሉ ቁልፍ የጁንታው አመራሮች አዲስ አበበ መግባታቸው ይታወሳል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል።

ዶክተር አረጋዊ በርሄ እንዳሉት፤ የህወሃት ጁንታ የፌደራል መንግስት ስልጣንን ተቆጣጥሮ በቆየባቸው ጊዜያት በኢትዮጵያውያን ላይ አስከፊ ግፍና ሰቆቃ ፈጽሟል።

ጽንፈኛ ቡድን የተጀመረውን ለውጥ ባለመቀበል ወደ መቀሌ ከሸሸ በኋላም ቢሆን ኢትዮጵያን ለማተራመስ በርካታ እኩይ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱንም አንስተዋል።

ይህ አልበቃ ብሎት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ አሳፋሪ ክህደት ፈጽሟል ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል።

በመሆኑም የጥፋት ሴራ ጠንሳሽ የሆኑት የጁንታው ቁልፍ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ለዘላቂ ሰላምና የህግ የበላይነት መከበር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዴሞክራሲ፣ አብሮነትና አንድነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑንም አክለዋል።

የኢዜማ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው የጥፋት ቡድኑ መንግስት በተደጋጋሚ ያቀረበውን የሰላምና እርቅ ጥሪን ወደ ጎን በመተው ዜጎች የተረጋጋ ህይወት እንዳይመሩ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

የቡድኑ የበላይ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ደግሞ በኢትዮጵያ ተደቅነው የነበሩ የጥፋት እቅዶች እንዲከሽፉ አድርጓል ነው ያሉት።

የተወሰደው እርምጃ የትግራይ ህዝብን ከበይ ተመልካችነት አውጥቶ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርዓት እንዲዘረጋ እድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

ጁንታው የገጠመው ኪሳራ "ስልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል ውድቀጥን እንደሚያፋጥን ትምህርት የሰጠ ነው" ሲሉም ነው የተናገሩት።

በቅርቡ የህወሃት የጥፋት ሴራ ስትራቴጅስት ስብሃት ነጋና የቀድሞው የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳደር አባይ ወልዱን ጨምሮ በርካታ የጁንታው አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና ሌሎች የፌደራል ጸጥታ ተቋማት በጋራ በመሆን እያከናወኑት ያለውን ወንጀለኞችን የማደን ዘመቻ አጠናክረው እንደቀጠሉም ይፋ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም