ቀጥታ፡

የአምራቾችንና ላኪዎችን አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ የአሰራር ማሻሻያዎች እየተዘረጉ ነው...ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

ሐዋሳ፤ጥር 5/2013 (ኢዜአ) የሃገሪቱን የወጭ ንግድ ለማሳለጥ እንዲቻል የአምራቾችንና ላኪዎችን አቅም የሚያሳድጉ የአሠራር ማሻሻያዎች እየተዘረጉ መሆኑን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተመራ ልዑክ በደቡብና በሲዳማ ክልሎች ከሚገኙ አምራቾችና ላኪዎች እንዲሁም የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ጋር በዘርፉ ለሚያገጥሙ ማነቆዎች የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ በሐዋሳ መክሯል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የውጭ ንግድ ግብይትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ አሰፋ ሙሉጌታ በወቅቱ እንዳሉት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የወጭ ንግድን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በተለይ የአምራችና ላኪዎችን አቅም ለማሳደግ የሚረዱ የአሠራር ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከተደረጉ ከማሻሻያዎች መካከል በወርቅና በሌሎች ማዕድናት ህገ ወጥ ግቢይትን ለመግታት የተደረገው የፖሊሲ ማዕቀፍ ማሻሻያና የአሠራር ለውጥ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቡናና የጥራጥሬ የመሳሰሉ የግብርና ምርቶችን ከብክነት ለመከላከልና ዘመናዊ ግብይትን ለማስፈጸም በተከናወነ የአሰራር ማሻሻያ ውጤት እየተገኘ መሆኑንም አመልከተዋል።

የምርት ተቀባዮች አካባቢ የሚፈጠረውን ችግር በመፍታት አምራችና ላኪዎችን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግና ባለድርሻ አካላትን የሚያስተሳስር የውል የአስተዳደር ሥርዓት እንዲዘርጋ መደረጉን አብራርተዋል።

የአሠራር ማሻሻያዎቹ በክልሎችና በሌሎች የመንግስት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች መካከል ተቀራርቦ  የመሥራት ልምድ በማዳበር ችግሮች በአጠረ ጊዜ እንዲፈቱ የሚያደርጉ እንደሆኑም አመልክተዋል።

የንድግ ሥርዓቱን ከባህላዊ አሠራር የማላቀቅና ዘመናዊ አሠራርን የተከተለ እንዲሆን የሚያስችሉ አሰራሮች እየተዘረጉ እንደሆነም ተናግረዋል።

ነጋዴው ቤቱ ሆኖ ፈቃድ የሚያወጣበትና የሚያድስበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ድካምንና ልፋትን የሚቀንሱ፣ ጊዜና ጉልበት የሚቆጥቡ አሠራሮች ለመዘርጋት የሚያስችሉ ህጎች መጠናቀቃቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ከበጀት አመቱ አጋማሽ ጀመሮ የኤሌክትሮኒከስ የንግድ አሠራርን ወደ ተግባር ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ አሰራሩ አምራቾች፣ ላኪዎች እንዲሁም የንግዱን ማህበረሰብ የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል።

 "ከመንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት የተለያዩ ድጋፎችን ለማግኘት በሚፈለግበት ጊዜ አሰልቺና ለእንግልት የሚዳርጉ አሠራሮች መኖራቸውን የገለጹት ደግሞ  የሽመና ምርቶችን ወደ ውጭ ሃገራት በመላክ ንግድ የተሰማራው የጃኖ ዕደ ጥበብ ኢንተርፕራይዝ ሰብሳቢ አቶ ፍሬው ቆንጆ ናቸው።

የግብአት እጥረቶች ዘርፉን እየተፈታተነ እንደሆነም  አመልክተዋል።

የአሰራር ማሻሻያው ችግሮቹን በመፍታት ዘርፉን በማጠናከር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግ ይረዳል የሚል እምነት

እንዳላቸው ምተናግረዋል

"መንግስት አምራቾችና ላኪዎች ያለባቸውን ችግር ለመፈታት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ  ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል

የደቡብ ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አሸናፊ ፈለቀ በበኩላቸው "በክልል የሚገኙ የአስመጪዎችንና ላኪዎችን ሚና ጠንካራ ለማድረግ መንግስት በቅርበት መሥራት አለበት "ብለዋል።

የነጋዴውን ውጤታማነት የሚፈታተኑ የአሠራር ክፍተቶችን በዘላቂነት ለማረም የተሰጠው ትኩረት ተስፋ የሚሰጥ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው ምክር ቤቱ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተርና የልዑካን ቡድኑ መሪ አቶ ስለሺ ለማ የግሉ ዘርፍ መሪ ተዋናይ በሆነባቸው ዘርፎች ለውጦች እየተመዘገቡና ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።

"ዘርፉን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በአምራች ዘርፎች መካከል ቅንጅታዊ አሠራርን ማሻሻል ላይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል" ብለዋል።

በባለሃብቶች፣ በክልልና በፌዴራል ደረጃ ሊፈቱ የሚገባቸውን ጉዳዮች በመለየት በተሳለጠ አሠራር መፍትሄ ለማበጀት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

የውይይት መድረኩም በዘርፉ የተያዘውን ግብ በተደራጀ አግባብ ለመመለስ በየደረጃው አቅም ለመፈጥር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ልዑክ አባላት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክና የይርጋለም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም