የመተከልን ሠላም ለመመለስና የጥፋት ቡድኑን ለሕግ ለማቅረብ ከሕዝቡ ጋር እንሰራለን - አዲሶቹ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የመተከልን ሠላም ለመመለስና የጥፋት ቡድኑን ለሕግ ለማቅረብ ከሕዝቡ ጋር እንሰራለን - አዲሶቹ አመራሮች
አዲስ አበባ፣ ጥር 5/ 2013 (ኢዜአ) በመተከል ዘላቂ ሠላም እንዲመለስና የተደራጀው የጥፋት ቡድን ለሕግ እንዲቀርብ ከሕዝቡና ከፀጥታ አካሉ ጋር እንደሚሰሩ በዞኑ የተመለመሉ ተተኪ አመራሮች ተናገሩ።
በፌዴራል መንግስት የተቋቋመው ግብረ ሃይል በዞኑ ከሚከውናቸው ተግባራት መካከል የመንግስት መዋቅሮችን መፈተሽና ከጥፋት ቡድኑ ጋር ሲሰሩ የነበሩ አመራሮችን ለሕግ ማቅረብ አንዱ ነው።
በዞኑ በተፈጠረው የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በተሳተፉ፣ ችግሩን ቀድሞ መፍታት እየተቻለ ዝምታን በመረጡና በቸልተኝነት በተጠረጠሩ አመራሮች የተተኩ አመራሮች የሕዝቡን ይሁንታ አግኝተው የሥራ አቅጣጫ ተቀብለዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ተተኪ አመራሮች በዞኑ ለተፈጠረው ችግር መባባስ ለረዥም ጊዜ ማንነትን መሰረት ያደረጉ የተዛቡ ሃሰተኛ መረጃዎች መሰራጨት፣ የአመራሩ ቸልተኝነትና የአመለካከት ችግሮችን ይጠቀሳሉ።
በተለይም ከአገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ "የለውጡ ኃይል አፋኝ፣ የብሔር መብት የማያከብርና ጨፍላቂ ነው" በሚል ሕዝቡን በመቀስቀስ ወዳልተገባ ተግባር እንዲገባ ግፊት መደረጉን ተናግረዋል።
በዞኑ የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን በብሔር በመለያየት ለማጋጨት ስራዎች መሰራታቸውንም ነው ያነሱት።
ይህን ተከትሎ በሕዝብ ላይ ጥቃት የሚፈፅም ቡድን ያደራጁ አካላት መኖራቸውን የገለጹት ተተኪ አመራሮቹ በዚህ መልኩ ጥቃት እንዲፈፀም መደረጉንም ጠቅሰዋል።
አሁን የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ከመንግስት ሠራተኛው ጀምሮ አስከ ሕዝቡ ድረስ ሰፊ የግንዛቤ መፍጠሪያ ሥራዎችን ለመስራት መዘጋጀታቸውንም ተተኪ አመራሮቹ ገልፀዋል።
በዜጎች ላይ ጥቃት እንዲፈፅም የተደራጀውን ቡድን ለማደን በሚደረገው እንቅስቃሴ ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው ተሳትፎ እንደሚያደርጉም እንዲሁ።
በተደራጀው ቡድን ጥቃት ሳቢያ ሕዝቡ ወደ ጥርጣሬ መግባቱን ጠቁመው፤ በህዝቦች መካከል መተባበርና አብሮነትን እንዲጎለብት እንደሚሰሩም ነው የገለጹት።
በዞኑ የተከሰተው የጸጥታ ችግር እንዲቀጥል የሀሰት መረጃ የሚያሰራጩ ሃይሎችን እንደሚታገሉም ተናግረዋል።
የደረሱ ሰብሎችን እንዲሰበሰብ ማድረግም ቀዳሚ ተግባራቸው እንደሚሆንም ገልፀዋል።