ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ወደ ዩኒቨርሲቲነት አደገ

አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ወደ ሙሉ ዩኒቨርሲቲነት ማደጉን ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ምዘና ኤጀንሲ ፈቃድ በማግኘት ወደ ሙሉ ዩኒቨርሲቲነት መሸጋገሩን አስመልክቶ የእውቅናና የምስጋና መርሃ-ግብር አከናውኗል።

በመርሃ-ግብሩ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነአ ያደታ፣ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮችና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መስፍን አበበ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር የቴክኖሎጂ እድገትን ተከትሎ በየወቅቱ እየተስፋፉና እየተወሳሰቡ የመጡ ወንጀሎችን በብቃት ለመወጣት ሁለንተናዊና ሙያዊ ብቃት መላበስ ይገባል ብለዋል።

ለዚህም በሕግ ማስከበር፣ በወንጀል መከላከልና የዜጎችን ደህንነት ከስጋት ለመጠበቅ የፖሊስ ትምህርትና ስልጠናን ማሻሻልና ማዘመን ማስፈለጉን ገልጸዋል።

"የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ወደ ሙሉ ዩኒቨርሲቲነት መሸጋገሩም በወቅታዊ አገራዊ የፖሊስ ተልዕኮ ውስጥ የሚገባን ድርሻ  በብቃት ለመወጣት ትልቅ መሰረት ነው" ብለዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ወደ ሙሉ ዩኒቨርሲቲነት መሸጋገሩ የአገሪቷን የፖሊስ አገልግሎት በምርምርና በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በተሰጠው ደረጃ ልክ ጥራት ያለው ጥናትና ስልጠና እንዲሁም የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ድጋፍ  እንደሚደረግለትም አረጋግጠዋል።

የሠላም ሚኒስትር ዴኤታና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ስዩም መስፍን ባስተላለፉት መልዕክትም ዩኒቨርሲቲው ነባራዊ ሁኔታን በተከተለ መልኩ ለሙያው የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ ይሆናል ብለዋል።

በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ እንዲሆንና ሁለንተናዊ ሪፎርም እንዲያጠናክር አሳስበዋል።

ለዩኒቨርሲቲው እድገት አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፌዴራልና የክልል አጋሮች፣ ግለሰቦችና የውጭ ተቋማት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።

ዩኒቨርሲቲው በ1939 ዓ.ም አባዲና ፖሊስ ኮሌጅ በሚል ስያሜ ተቋቁሞ የኮሚሽኑ አንጋፋ የትምህርት ተቋም ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ሲሆን ከ1967 እስከ 1999 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ፤ ከ1999 ዓ.ም እስካሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሚል ስያሜ ነበረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም