የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ወደ ሙሉ ዪኒቨርሲቲነት አደገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ወደ ሙሉ ዪኒቨርሲቲነት አደገ
አዲስ አበባ፣ ጥር 4/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ወደ ሙሉ ዪኒቨርሲቲነት አደገ።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ምዘና ኤጀንሲ ፈቃድ በማግኘት ወደ ሙሉ ዩኒቨርሲቲነት መሸጋገሩን አስመልክቶ የእውቅናና የምስጋና መርሃ-ግብር አከናውኗል።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዘደንት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መስፍን አበበ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በየወቅቱ እየተስፋፉና እየተወሳሰቡ የመጡ የረቀቁ ወንጀሎችን ብቃት ባለው የምርመራ ስራ ለመወጣትና ወንጀለኞችንም ለህግ ለማቅረብ ሙያዊና ሁለንተናዊ ብቃት መላበስ ያስፈልጋል።
ለዚህም በህግ ማስከበር፣ በወንጀል መከላከልና የዜጎችን ደህንነት ከማንኛውም ስጋት ለመጠበቅ የትምህርት ስርአትን ማሻሻልና ማዘመን ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ወደ ሙሉ ዩኒቨርሲቲነት መሸጋገሩ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ወደ ሙሉ ዩኒቨርሲቲነት መሸጋገሩ የአገሪቱን የፖሊስ አገልግሎት በምርምርና በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በ1939 ዓ.ም አባዲና ፖሊስ ኮሌጅ በሚል ስያሜ የኮሚሽኑ አንጋፋ የትምህርት ተቋም ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ሲሆን ከ1967 እስከ 1999 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ፣ ከ1999 ዓ.ም እስከ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሚል ስያሜ ሲጠራ ቆይቷል።
በመርሃ-ግብሩ የመከላከያ ሚኒስቴሩ ዶክተር ቀናኢ ያደታን ጨምሮ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።